Fana: At a Speed of Life!

ለሚቀጥሉት 5 ወራት የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪም ሆነ ተከራዮችን ማስለቀቅ የተከለከለ ነው – የድሬዳዋ ከተማ  አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት አምሥት ወራት የመኖሪያ ቤት አከራዮች በተከራዮቻቸው ላይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪም ሆነ ከቤት የማስለቀቅ ተግባር እንዳያደርጉ ውሳኔ አሳልፏል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ ሰኔ 2 ቀን 2014 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ሁለት ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን ፣ ውሳኔዎቹን አስመልክቶ የአስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ  አቶ ብሩክ ፈለቀ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።

በመግለጫቸውም  በድሬዳዋ አስተዳደር የዝናብ ወቅት መራዘምን ተከትሎ በገጠር ቀበሌዎች ላይ የከፋ ድርቅ እንዳይከሰት ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመውየዳሰሳ ጥናት መሰራቱን አንስተዋል፡፡

በጥናቱ ውጤት መሠረትም ÷  በግብርናው ዘርፍ የእንስሳት መኖ ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረቶች እና በጤናና ትምህርት ዘርፎች ላይ ደግሞ ከድርቁ ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸው እንደተለዩ ነው የገለጹት፡፡

የጥናቱን ውጤት ተከትሎም ችግሮች እንዳይባባሱ የአስተዳደሩ ካቢኔ የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፋቸውን አቶ ብሩክ ፈለቀ ተናግረዋል ።

በውሳኔው መሠረትም ÷ አርሶአደሩ ወቅቱን ጠብቆ ቢዘራም የተዘራው ዘር ባልበቀለበት ቦታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ አዝዕርት ተገዝተው ለአርሶ አደሩ እንዲከፋፈሉ ፣ ለእንስሳት የመኖና የመድሐኒት አቅርቦትም  በፍጥነት ይቀርባል ተብሏል፡፡

በተለይ የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ተጨማሪ የውሃ ቦቴዎች በመጠቀም ውሃ እንዲደርስላቸውና በተፈጠረው ችግር ምክንያት ዜጎች እንዳይጎዱ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ የአስተዳደሩ ካቢኔ መወሰኑን አቶ ብሩክ ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ዐብይ ኮሚቴ በማቋቋም ለችግሩ ምላሽ እንዲሰጥ 10 ሚሊየን ብር በጀት ፀድቆ መመደቡንም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም አስተዳደሩ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ  የቤት አከራዮች  በተከራዮቻቸው ላይ  አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉና ከጭማሪ ጋር ተያይዞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ ያለውን ተከራዮችን የማንገላታት ጭማሪ መክፈል ያልቻሉ ከቤት የማስወጣት ተግባር እስከ ሚቀጥሉት 5 ወራት እንዲያቆሙ ውሳኔ መተላለፉም የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን በመረጃው አመላክቷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.