Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል ለ3 ሺህ 673 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4 ፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለ3 ሺህ 673 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል፡፡
 
የክልሉ መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ ለሕግ ታራሚዎቹ ይቅርታ የተደረገው በ1994 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 57(3) (i) እና የይቅርታ ሥነ ስርዓት ማስፈጸሚያ አዋጅ ቁጥር 114/1998 አንቀፅ 12(2) ለክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መሆኑን ገልጿል፡፡
 
በዚህ መሰረትም 3 ሺህ 419 ወንድ እና 254 ሴት በድምሩ 3 ሺህ 673 የሕግ ታራሚዎች ከማረምያ ቤት እንዲለቀቁ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መወሰናቸው በመግለጫው ተመላክቷል፡
 
መግለጫው አክሎም፥ የህግ ታራሚዎቹ ከጥፋታቸው ተምረውና ታርመው፣ የህዝባችንን እሴት ተላብሰው፣ መልካምና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ይቅርታ እንዳደረጉላቸው ነው የገለጸው።
 
በይቅርታ ከማረምያ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው የህግ ታራሚዎች በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ከተፈረደባቸው መካከል 12 ዓመትና ከዚያ በላይ ፍርድ ያጠናቀቁ፣ በፅኑ እስራት እድሜ ልክ ተፈርዶባቸውና ይቅርታ የማያሰጥ ፣ በማንኛውም ዓይነት የግድያ ወንጀል ከተሳተፉ ውጪ ከ3 ወር ቀላል ፍርድ እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት ከተፈረደባቸው ውስጥ 1/3ኛውና ከዚያ በላይ የፈፀሙትን እንደሚያካትትም ተገልጿል፡፡
 
በኢፌዴሪ እና በኦሮሚያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 28 መሠረት የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው፣ በጥልፊያ ፣ በአስገድዶ መድፈር ፣ በዝርፊያና ስርቆት ወንጀል የተፈረደባቸው ይቅርታው የማይመለከታቸው እንደሆነም ነው መግለጫው ያስታወቀው።
 
የክልሉ መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
ጠንካራ ሀገረ መንግስትና የተረጋጋ ማህበራዊ መስተጋብር ለመፍጠር የይቅርታ እሴቶቻችንን ማጠናከርና ማጎልበት እጅጉኑ አስፈላጊ ነው። በይቅርታ መሻገር፣ በፍቅር መደመር ማህበራዊ ስብራቶቻችንን ለመጠገን፣ ነገያችንን በጥሩ መሰረት ላይ ለመገንባት ያለመ አገር በቀል እስቤያችን ነው።
 
የኦሮሞ ህዝብ ቅራኔ ሲፈጠር እና ወንጀል ሲፈጸም ተጎጂ የሚካስበት፣ አጥፊው የሚማርበት፣ ማህበራዊ መስተጋብር ሳይናጋ እርቀሰላም የሚፈጠርበት፣ ፍትህ ሳይጓደል የሚያሰፍንበትን ስርዓት ፈጥሮ እርስ በርሱና ከሌላው ወንድም ህዝቦች ጋር ሲዳኝበት ኖሯል።
 
ህዝባችን ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥበት አያሌ የእርቅ ባህል አለው። የጉማ ሥነ ስርዓትን በመፈጸም ቅራኔን ያርቃል፣ እንባን ያብሳል፣ ማህበራዊ መስተገብር ሳይዛነፍ ፍትህን በዘላቂነት ያሰፍናል። ይህን በታሪክ ሂደት የተጎናጸፍነዉን ድንቅ እሴት ማጎልበትና ማህበራዊ ስብራቶቻችንን ለመጠገን ልንጠቀምበት ይገባል።
 
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ወደ ቀደምት ‘ባህላችንና እሴቶቻችን እንመለስ’ በሚል መርህ ፈረጀ ብዙ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ባህላዊ መዳኛዎችን በማቋቋምና በማደራጀት ፍትህን ተደራሽ፤ ህዝባችንን ከእንግልት ለመታደግ በመስራት ላይ ይገኛል።
 
በዚሁ መሰረት የህግ ታራሚዎች ከጥፋታቸው ተምረውና ታርመው፣ የህዝባችንን እሴት ተላብሰው፣ መልካምና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስዳድር ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለ3,673 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጎላቸዋል።
 
ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎቹ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በቆዩበትጊዜ ጥሩ ሥነ ምግባር ያሳዩና በህግ በተደነገገው የይቅርታ መስፈርትን ያሟሉና በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረቡ ናቸው።
 
የተሠጠው ይቅርታ በ1994 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ ህገ መንግሥት አንቀፅ 57(3) (i) እና የይቅርታ ሥነስርዓት ማስፈጸሚያ አዋጅ ቁጥር 114/1998 አንቀፅ 12(2) ለክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር በተሠጠው ሥልጣን መሠረት ነው።
 
በመሆኑም፣ 3,419 ወንድ እና 254 ሴት በድምሩ 3,673 የህግ ታራሚዎች ከማረምያ ቤት እንዲለቀቁ ተወስኗል።
 
በይቅርታ ከማረሚያ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው የህግ ታራሚዎችም በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ከተፈረደባቸው መካከል 12 አመትና ከዚያ በላይ ፍርድ ያጠናቀቁ፣ በፅኑ እስራት እድሜ ልክ ተፈርዶባቸውና ይቅርታ የማያሰጥ ፣ በማንኛውም አይነት የግድያ ወንጀል ከተሳተፉ ውጪ ከ3 ወር ቀላል ፍርድ እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት ከተፈረደባቸው ውስጥ 1/3ኛውና ከዚያ በላይ የፈፀሙትን ያካትታል።
 
በኢፌዴሪ እና ኦሮሚያ ህገ መንግሥት አንቀፅ 28 መሠረት የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው፣ በጥልፊያ ፣ በአስገድዶ መድፈር ፣ በዝርፊያና ስርቆት ወንጀል የተፈረደባቸው ይቅርታው የማይመለከታቸው ይሆናል።
 
ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች በማንኛውም ወንጀል ተመልሰው ተሳትፈዉ ከተገኙ የተሰጠው ይቅርታ የለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚነሳና በህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
 
ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት
 
ሰኔ 4/2014
 
ፊንፊኔ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.