Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ሚኒስቴር ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቅንጅት ለመስራት የሚያግዘውን ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ – ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሰላምና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የምክክር፣ የስልጠና እና የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ የፀጥታ እና ፍትህ አካላትን አቅም ግንባታ ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡

ስምምነቱ ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቅንጅት ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ገልጸዋል፡፡

ምርጫው ዜጎች በህገ-መንግስቱ የተቀመጠላቸው መብት ተከብሮላቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው እንዲረጋገጥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው የፌደራል፣ የክልሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መጭው ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ በሁሉም እርከኖች የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ሁለንተናዊ አቅም ለመገንባት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታዋ ምርጫው ለመላው አፍሪካ ምሳሌ ሆኖ የሚያልፍ እንዲሆን ለማስቻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

የጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረሥላሴ በበኩላቸው፥ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች በሌሎች እንዳይጣሱ ህገመንግስታዊና ተፈጥሯዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ተግባር ከሁሉም የሚጠበቅ የሞራል ግዴታ መሆኑን አውስተዋል።

የፀጥታ እና ፍትህ አካላትን አቅም የመገንባት ተግባራትን ለማከናወን የሚውል የ27 ሚሊየን ብር በጀት መመደቡን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.