Fana: At a Speed of Life!

የአፋርና የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋርና የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ የሰላም ውይይት ማጠቃለያ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
መድረኩ በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል።
በውይይቱ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሁለቱ ክልሎች ዑጋዞች፣ ጋራዶችና የሃገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ ብናልፍ አንዱዓለም÷ የአፋርና የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰለጠነ መንገድ ተነጋግረው መቋጫ የሚፈጥሩበት በዘመናት የተገነባ ባህላዊ ሥርዓት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሰላም ውይይቱ ማህበረሰቦቹ በሰላማዊ ግንኙነት አብረው እንዲኖሩ ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡
የሰላም ውይይቱ የተጋጩ ሰዎችንም ሆነ ቡድኖችን በማወያየት በዜጎች ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ለመከላከል ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ሁለቱ ክልሎች ሲያደርጉ የነበረው ተከታታይ ውይይት ማጠቃለያና የጋራ ስምምነት ላይ የሚደረስበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መድረኩ በአካባቢዎቹ የሚታዩትን አለመግባባቶች በውይይት በመፍታት ሰላምን ለማምጣት ወደ ግጭት ለሚያመሩ ጉዳዮችም መፍትሔዎች ተለይተው የሚቀመጡበት መሆኑን ከሰላም ሚኒስቴር ያገነነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይ የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ ማድረግ፣ በግጭት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያ እና በዘመድ ቤት ተጠልለው እየኖሩ ችግሮችን እየተጋፈጡ ያሉ ወገኖች ወደ ቀደመው ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሚያግዙ ጉዳዮችም ተመላክተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.