Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ በተለያየ ዘርፍ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር መላውን ሕዝብ በማሳተፍ ለመመከት ጥረት ተደርጓል-አቶ ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በ2014 በጀት ዓመት በተለያየ ዘርፍ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር መላውን ሕዝብ በማሳተፍ ለመመከት ጥረት መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ገለጹ።
 
በደቡብ ክልል በ2014 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም እና በ 2015 እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እየተካሔደ ነው፡፡
 
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ÷ ባሳለፍነው የ2014 በጀት ዓመት በዋናነት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች እንደ አገር የተቃጣብንን ወረራ መመከት እንዲሁም የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነበር ብለዋል።
 
ለዚህም መላው የክልሉ ሕዝብ እና የጸጥታ ኃይሉ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያብራሩት።
 
በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ በስልጤ ዞን በሃይማኖት ሽፋን የተከሰተ ችግር፣በደቡብ ኦሞ ዞን ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ ደግሞ በአመራሩ እና በጸጥታ ኃይሉ ላይ የደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በአብነት ጠቅሰዋል።
 
በክልሉ በተለያየ ዘርፍ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር መላውን ሕዝብ በማሳተፍ ለመመከት ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል።
 
በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ሀሳቦች የተንጸባረቁበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በተለይ ስንዴን በበጋ መስኖ በማልማት ረገድ የተገኘው ውጤት ስኬታማ እንደነበር አስረድተዋል።
 
በክልሉ በምርጥ ዘር እና በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት መደረጉን ጠቁመው÷ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ዝግጅ እና ተከላ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
 
የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መጓተት ችግር ቢስተዋልም የተወሰኑ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉንም ገልጸዋል።
 
የበጀት እጥረት እና እየተስተዋለ የነበረው የጸጥታ ችግር ለፕሮጀክቶቹ መጓተት መንስኤ እንደነበርም ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ጠቁመዋል።
 
በውይይት መድረኩ የክልሉ የካቢኔ አባላት እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.