Fana: At a Speed of Life!

አይ ኦ ኤም በሶማሊያ ለሚያከናውነው ሰብዓዊ ድጋፍ 66 ሚሊየን ዶላር ጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በሶማሊያ ለማደርገው የሰብዓዊ ድጋፍ 66 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልገኛል ማለቱ ተገለጸ፡፡

ድርጅቱ በሶማሊያ 1 ነጥብ 25 ሚሊየን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው እና ለዚህም እስከ ፈረንጆቹ የካቲት 2023 ባለው ጊዜ 66 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡

በሀገሪቱ ከተከሰተው ድርቅ መባባስ ጋር ተያይዞ ሶማሊያውያን ከሚደርስባቸው መከራ በፍጥነት ለመታደግ ፈንዱ በአስቸኳይ ሊለቀቅልኝ ይገባል ሲል ድርጅቱ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ ለጋዜጠኞች በሠጠው መግለጫ መጠየቁ ነው የተመለከተው፡፡

ተመድ የሶማሊያውያን ግማሽ ያህሉ ዜጎች (7 ነጥብ 1 ሚሊየን ሶማሊያውያን) ለድርቅ አደጋው ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

ባሳለፍነው አርብ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት “ ኦቻ” በፈረንጆቹ 2022 ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሶማሊያውያን 260 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማግኘቱን አረጋግጧል፡፡

በድጋፉም 2 ነጥብ 8 ሚሊየን እየተባባሰ በመጣው የድርቅ አደጋ የተጎዱ ሶማሊያውያንን ሕይወት መታደግ መቻሉን ነው ያስታወቀው፡፡

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት “አይ ኦ ኤም” በበኩሉ በድርቅ የተጎዱ ከ 350 ሺህ በላይ ሶማሊያውያንን እስከ አሁን መርዳት እንደቻለ እና በቀጣይም አገልግሎቱን እንደሚያሳድግ አረጋግጧል፡፡

ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ በድርቁ ምክንያት 800 ሺህ ያህል ሶማሊያውያን መፈናቀላቸውንና ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡

በሶማሊያ መዝነብ የነበረበት ወቅታዊ የክረምት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ ዜጎች ለከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ዕጥረት እና 3 ሚሊየን ለሚደርሱ እንስሳቶቻቸው ሞት ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በተጨማሪም በዓለም አቀፋዊው ወቅታዊ ሁኔታ እና በሀገሪቷ እየተባባሰ በመጣው ድርቅ ምክንያት በሀገሪቷ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱንም ነው “አይኦ ኤም” ያመላከተው፡፡

ድርጅቱ የምግብ ዕጥረት እና ዋጋ መወደድ፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግር፣ የጤና ክብካቤ ማጣት እና የመጠለያ ችግር በሶማሊያ በፍጥነት መፈታት ያለባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡

አሁን ላይ በሃገሪቱ 213 ሺህ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን እና ሺንዋ ዘግበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.