Fana: At a Speed of Life!

በአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ላይ የዋጋ ማስተካከያ እንደሚደረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራሉ መንግስት ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ 15 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን ተከትሎ በአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ላይ የዋጋ ማስተካከያ እንደሚደረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ክልሉ ለ2014/15 ምርት ዘመን ካቀደው የአፈር ማዳበሪያ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ወደ ክልሉ ገብቶ እየተሰራጨ እንደሚገኝ የክልሉ የግብርና ግብዓቶችና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ተናግረዋል።

ወደ ኀብረት ስራ ማህበራት ከ3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ የተጓጓዘ ሲሆን÷ እስካሁን 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን ተናግረዋል።

የፌደራል መንግስት ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ 15 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን ገለጸው÷ ይህን ተከትሎ በአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ላይ የዋጋ ማስተካከያ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

አፈፃፀሙን በተመለከተ ግብርና ሚኒስቴር በሚያወርደው አሠራርና አቅጣጫ መሠረት የሚፈፀም ይሆልም ነው ያሉት፡፡

አቅርቦትና ስርጭቱን ፍትሐዊ ለማድረግ፣ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ቢሮው ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው÷ አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች ሲኖሩ በወቅቱ እንዲስተካከል እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ምርጥ ዘር በተለይ የበቆሎ ሰብል ቀድሞ የሚዘራ በመሆኑ፥ ከቀረበው 93 ሺህ 869  ኩንታል ውስጥ እስካሁን 76 ሺህ 667 ተሠራጭቷል ማለታቸውን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የአፈር አሲዳማነትን በማከም ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው “ኖራ” ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ሲሆን÷ ከቀረበው 39 ሺህ 327 ኩንታል ኖራ ውስጥ 21 ሺህ 495 ኩንታል መሰራጨቱን ገልፀዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.