Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ አዳምጧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየሰጡት ባሉት ምላሽ÷ ባለፉት አራት ዓመታት የተከሰቱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ልናሳካው ያሰብነውን ዕቅድ በታሰበለት ልክ እንዳይሄድ አድርገውታል ብለዋል፡፡

ያልተገነባ ሰው ተቋም አይገነባም፤ ያልተገነባ ተቋም ደግሞ ሀገር አይገነባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ የሰው ልጅ ለሀሳብ ክብር ሊሰጥ እና ዘር የማያመክን ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተሰጠው ጊዜ የማይጠቀም አካል ትርፉ ጸጸት መሆኑን ገልጸው÷ ሁሉም አካላት የጊዜ አጠቃቀምን ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም ሁሉም ጣት ከመቀሳሰር ይልቅ ወደ ራሱ በማየት በተሰማራበት መስክ ጊዜን በአግባቡ ሊጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ሰው ራሱን ብሎን አካባቢውን ለማልማትና ለማሳደግ ቁርጠኛ ካልሆነ ለሀገር ልማት ተባባሪ ሊሆን አችልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ስለሆነም ችግርን ሲተነትኑ ከመኖር ይልቅ ሁሉም ሰው ለሀሳብ፣ ለጊዜ እና ከራሱ ጀምሮ እስከ ሀገር ባሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ቁርጠኛ እና ተባባሪ መሆን ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ እንዲህ ሲሆን ችግሮቻችን ይቀላሉ፤ ዕድገታችን ይፋጠናል ብለዋል፡፡
የሚሠራ ሰው ጠዋት ቢወቀስም ማታ መሞገሱ እንደማይቀር ጠቁመው÷ የዛሬውን ወቀሳ ሳይሆን የነገውን ሙገሳ በማሰብ በትጋት መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የለውጡን ጉዞ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በትክክል መገንዘብና ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ ኮቪድ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ፣ ድርቅ ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች እንቅፋት መሆናቸውን አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም በሀገር ውስጥ የገጠመን ውጊያ ከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማስከተሉን ጠቅሰው፥ መፈናቀል እና ያልተገባ የውጪ ጫና እንዲሁም የሀገር ውስጡ ሁኔታ ጋብ ሲል የዩክሬን እና የሩሲያ ግጭት ያስከተለው ዓለም አቀፍ ጫና ተጋላጭ ሆነናልም ነው ያሉት በማብራሪያቸው።
ከዚህ አንጻርም “የገጠሙንን ፈተናዎች እንዴት አለፍናቸው የሚለውን ማየት” አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል።
የተደረገው ውጊያ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የመታደግ ሥራ እንደነበር ማስታወስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ፥ ለብልጽግና መሰረቶችን ጥለናል ነው ያሉት።
“ይህ ሁሉ ፈተና እንደ መንግሥት፣ እንደ ፓርቲ በወጉ ሳንደራጅ የገጠመን ችግር መሆኑን ታሳቢ ማድረግ” እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
ከመንገድ አውታር ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽ ከለውጡ በፊት ሀገር አቀፍ ሽፋኑ 127 ሺህ ኪሎ ሜትር መሆኑን ገልጸው ከለውጡ በኋላ ግን 165 ሺህ ኪሎ ሜትር መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 60 ሜትር ስፋት ያለው 151 ኪሎ ሜት በአስፋልት ደረጃ መሰራቱን እና ከአስፋልት ውጭ ደግሞ 470 ኪሎ ሜትር መንገድ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ውጭ በመላክ ከ82 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዶላር እንዲሁም ከቡና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከገበታ ለሀገር ጋር በተያያዘም÷ አራት አብያተ መጻሕፍት እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ ፕላንት ቤተ መጻሕፍት እና የማዕድን ቤተ መጻሕፍት መሆናቸውንም ዘርዝረዋል፡፡
ይህም እኛ ያላገኘነውን ዕድል ልጆቻችን እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ከሳይንስና ከዓለም ጋር ያላቸው ትውውቅ ይዳብራል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋጋ ውድነትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ ለኑሮ ውድነቱ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ችግሮቹን ለምፍታትም ብዙ ጥረት ተድርጓል ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነቱን የከፋ የሚያደርገውም መግዛት የማይችለውን ድሃውን የህብረተሰብ ክፍል ስለሚጎዳ ነው ብለዋል፡፡
የምርት እጥረት እና የፍላጎት ዕድገት፣ የንግድ ሥርዓት መዛባት፣ ምርቱ እያለ ማቅረቢያው ሎጅስቲክስ አለመኖር፣ ግጭት፣ መፈናቀል እንዲሁም የፋይናንስ አጠቃቀም በዋናነት እንደ ችግር የሚጠቀሱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃም የኑሮ ውድነቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸው÷ ቬንዙዌላ 1 ሺህ 198 ከመቶ፣ ሱዳን 340 ከመቶ፣ ሊባኖስ 201 ከመቶ፣ ሶሪያ 139 ከመቶ፣ አርጀንቲና 51 ከመቶ፣ ቱርክ 36 ከመቶ እንዲሁም በኢትዮጵያ 33 ከመቶ የዋጋ ግሽበት መኖሩን አብራርተዋል፡፡
ከሚቀጥለው ሀምሌ ወር ጀምሮ ለሕዝብ ትራንስፖርት መንግስት ድጎማ እንደሚያደርግም ነው ያስታወቁት፡፡
በዮሐንስ ደርበው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.