Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት በመሆኑ ኢትዮጵያ ሳታውቅ ድርድር የለም – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከህወሓት ጋር እስካሁን ድርድር ተጀምሯል የሚባለው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚቴው ሥራውን ሲያጠናቅቅ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ህወሓት የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት በመሆኑ ኢትዮጵያ ሳታውቅ ድርድር እንደሌለም አንስተዋል።
የጸጥታ ተቋማት ሁኔታን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ተቋሞቻችን ለህወሓት ብቻ አይዘጋጁም፤ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ነው የሚዘጋጁት ብለዋል፡፡
በአሁናዊ ሁኔታውም ከህወሓት የስልጣን ዘመን ጊዜ 3 እና 4 እጥፍ በላይ በቴክኖሎጂም ሆነ በቁጥር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ከህወሓት ጋር የተፈጠረው ግጭት መንስኤ ህወሓት የፖለቲካ ክስረቱን መንግስትን ለማፍረስ የሄደበት የኃይል አማራጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህን ለማሳካትም እስከ ሲኦል እንወርዳለን ማለታቸውን አስታውሰው፥ እኛ መዋጋት ሳይሆን እራሳችንን መከላከል ነው ያደረግነው ብለዋል።
በህወሓት አስተዳደር የትግራይ ሕዝብ ያተረፈው ጥላቻን ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁንም ችግርና ስደት እንዳለና አመራሮቹ የራሳቸውን ኑሮ የተሻለ ሊያደርጉ ቢችሉም ለሕዝቡ አለመስራታቸውን አውስተዋል።
ህወሓት ትግራይን ባስተዳደረበት ከሶስት ዓመታት በላይ ጊዜ ሕዝቡን እና አካባቢውን አለማልማቱን በመጥቀስም፥ ለልጆቻችን ሰላምን ማውረስ ይገባናል፤ ሀገር በጦርነት አታድግም ብለዋል በምላሻቸው።
ኢትዮጵያ በሀገራት መካከል ሰላም እንዲኖር አበክራ ትሰራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፥ ኢትዮጵያውያን ሰላም ወዳድ መሆናችንን ዓለም መስክሯል ብለዋል በማብራሪያቸው።
ውጊያ ከማንም ጋር አንፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሰላም ነው የምንፈልገው፡፤ ሰላም ደግሞ ትርፋማ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፍላጎት ግጭት እንዳይኖር ማድረግ መሆኑን በመጥቀስም፥ በሀገራት መካከል ሰላም ቢኖር ትርፉና ጥቅሙ ብዙ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ለዚህም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን ግጭት በሰላም እንዲተካ መደረጉን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያም ከራሷ አልፎ ለቀጠናው ሰላም አበክራ ትሰራለች፤ እየሰራችም ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፡፡
ከሳይበር ደኅንነት ጋር በተያያዘ 5 ሺህ 600 አካባቢ የቨርቹዋል ጥቃት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ሰላምን የሚያናጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር እየሠራን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሰላም የሚገኝ ድል ካለ ሰላም ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።
ከሕግ ማስከበር ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ ባለፈው ጉባኤ ሰላም፣ የዋጋ ግሽበት እና መልካም አስተዳደር ላይ በትኩረት እንደሚሠራ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውሰዋል፡፡
ከ1 ሺህ በላይ የሸኔ አባላት በኦሮሚያ ክልል መደምሰሳቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በአማራ ክልል የተወሰደው ሕግን የማስከበር ሥራ መቶ በመቶ በክልሉ ኃይል የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተሠራው የዘመቻ ሥራ የአማራ ክልልም ሆነ የምዕራብ ጎጃም ሕዝብ ደስተኛ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል በተወሰደው ሕግ ማስከበር ዘመቻ 3 ሺህ 500 ያህል ሰው በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው÷ ሁሉም የከዱ ሠራዊት መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከ2 ሺህ በላይ ያህሉ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ብዙ ኩንታል ሀሽሽ፣ ሕገ ወጥ ገንዘብ ሁሉ ተይዟል ብለዋል፡፡
በሌሎች ክልሎችም በሰላም፣ የኑሮ ውድነቱን በመቀነስ ረገድ ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
ለአማራም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚበጀው አንድነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተካሄደው ዘመቻ በስህተት የተያዘ እና አላግባብ የታሰረ ወይም የተጎዳ ሰው ካለ ምክር ቤቱ ኮሚቴ አቋቁሞ ማጣራት ይችላል ነው ያሉት፡፡
ከዘመቻው በኋላ በአማራ ክልል ሰላም መስፈኑን እና ዜጎች በሰላም እየኖሩ መሆኑን ገልጸው፥ የሕግ ማስከበር ሥራው በሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አጽንኦት ሰጥተዋል፤ ሕግን ማክበር ግዴታ መሆኑን በመጥቀስ።
በዚህ መሐል የተከበሩ ሙያዎችን ለወንጀል መደቢቂያነት መጠቀም በሕግ ያስጠይቃል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
ተረኝነትን በሚመለከት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ÷ ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ ቤት ነች፤ የአንዱ ብቻ ልትሆን አትችልም ብለዋል፡፡
‹‹ሀገርን እንደ እቁብ የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ፤ ቀጣይ አንተ ትመራለህ፤ ቀጣይ ደግሞ እከሌ ይመራል›› የሚል አስተሳሰብ እንደ ህወሓት የከሰረ አካሄድ ነው፤ ሁሉንም ያካተተ እንጅ የፈረቃ አካሄድ የለም ነው ያሉት በምላሻቸው፡፡
በአጠቃላይ ተረኝነት የለም፤ በካቢኔ አባላትም 6 አማራ፣ 6 ደቡብ እና 6 ኦሮሞ የሆነው በዚህ ጊዜ ነው ሲሉም ነው ያስረዱት።
በአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚኛ መዝሙር ተዘመረ ብሎ ቅሬታ ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ በመዲናዋ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ሲዘመር ምንም ያላለ ሰው፤ በኦሮሚኛ ተዘመረ ብሎ ሊከፋው አይገባም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ማለት የቋንቋ ብዝሃነትም ነው ብለዋል፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች የተወከሉ የሕዝብ ተወካዮችም ሕዝቡን የሚጠቅም ሥራ እንጅ የመበሻሸቅ ጉዳይ እያነሱ ማራገብ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
ሁሉን አካታች ውይይትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ ኮሚሽን የማቋቋም ስልጣን፣ አጀንዳ ማዘጋጀት እና ተሳታፊዎችን የመወሰን ስልጣንን ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት በኮሚሽኑ እንዲፈጸሙ ኃላፊነት መሰጠቱን አራርተዋል።
ሥራው አድካሚ ቢሆንም÷ ኮሚሽኑ በርካታ ችግሮችን እንደሚፈታም ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.