Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል አመራሮች በባህርዳር ከተማ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ከፍተኛ የመሰረተ ልማቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል አመራሮችን ጨምሮ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች በባህርዳር ከተማ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ትልልቅ መሰረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል፡፡

የባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት÷ የባህርዳርን ልማት ሁለንተናዊና ተደራሽ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ከራሱና ከዓለም ባንክ በሚመደብ የመቀናጆ በጀት ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው።

በተለይም በ2014 በጀት ዓመት ከዚህ በፊት በ3ኛ ወገን ሲጓተቱ የቆዩ መሰረተ ልማቶችን በውጤታማነት የተሰራበት ጊዜ መሆኑን አብራርተዋል።

በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በፌደራል መንግስት በተመደበ በጀት ትልልቅ መሰረተ ልማቶችና ግዙፍ ፋብሪካዎች መገንባታቸው ለማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴት ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በአመራር ስልጠና እና በጉብኝቱ የተሳተፉ የክልል፣ የምዕራብና የምስራቅ ጎጃም፣ የደቡብ ጎንደር የአዊ ዞኖች እንዲሁም የባህርዳር ከተማ አመራሮች ገልፀዋል።

አመራሮቹ በበኩላቸው÷ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ትልልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን በማየታቸው መደሰታቸውን ገልፀው በተለይም የመሰረተ ልማት ቦታዎችን ከ3ኛ ወገን ነፃ በማድረግ በኩል የተሄደበት ርቀት የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ነው የተናገሩት።

የዓባይ ድልድይ ከተቀናጀ የመንገድ ግንባታ ጋር የተጀመረውን ፕሮጀክት፣አዲሱ የዲያስፖራ የሆራይዞን የልደታና ባለእግዚአብሔር አስፋልት መንገዶች ፣ የልማት ፕሮጀክቶችና የእብነ በረድ ፋብርካዎች ከተጎበኙ ትልልቅ መሰረተ ልማቶች ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ከባህር ዳር ከተማ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.