Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ናይጄሪያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ በፖለቲካ፣ መከላከያ፣ በባህልና በቱሪዝም፣ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የተፈረመው ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየው ሦስተኛው የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ ነው።

ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻውል እና በናይጄሪያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሁመር ዘናባ ተፈራርመውታል።

አምባሳደር ፍስሃ ሻውል የመግባቢያ ስምምነቱ ፥ በርካታ ዓመታት ያስቆጠረውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የናይጄሪያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና አፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ቪክቶር አዱኩን በሁለቱ አገራት መካከል በመከላከያ፣ በጤና፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪ፣ ባህል፣ በቱሪዝም፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጅ፣ በአቪየሽን መስክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በመገናኛ ብዙሃን አስተዳደርና አመራር በተለይም የወጣቶችን ተሳትፎ በማሳደግና የፖን-አፍሪካዊነትን የሚዘክሩ ይዘቶችን ለማበልፀግ በሚቻሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት።

የመግባቢያ ስምምነቱ በኢትዮጵያና ናይጄሪያ መካከል ያለውን ፀጋ በመጠቀም ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት እንዲውል ያስችላል ተብሏል ።

ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በአፍሪካ ያለውን እምቅ የሰው ሀብት እና ገበያ በጋራ ማልማትና መጠቀም በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

አራተኛው የሁለቱ አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በፈረንጆቹ 2024 አቡጃ ከተማ- ናይጄሪያ እንደሚካሄድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.