Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የተጀመረው ሕግን የማስከበር ሥራ በተለያየ ወንጀል ተሰማርተው የነበሩ አካላትን ወደ ሕግ ያቀረበ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው የአማራ ክልል የአመራር ስልጠና ማጠቃለያ እና በቀጣይነት አመራሩ በሚሠራቸው ጉዳዮች ላይ በባሕርዳር ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ የክልሉ የልማት ድርጅቶች ዳይሬክተሮች፣ የሁሉም ቢሮዎች የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እና ሌሎች አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሽጥላ ፥ በየደረጃው ለሚገኙ የክልሉ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በውጤታማነት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዚህ የማጠቃለያ መድረክም አመራሮች የፓርቲና የመንግሥትን ትኩረት ተረድተው ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምሪቶችን የሚወስዱበት ይሆናል ፤ በቀጣይም የውስጥ አንድነትን አስጠብቀው እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

በመድረኩ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ ፥ “የአማራ ክልል አመራር ስልጠና ማጠቃለያ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ጽሑፍ አቅርበዋል።

አቶ እርዚቅ አመራሩ ከስልጠና በኋላ ይዞ መውጣት ያለበትን አቅጣጫዎች በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ፥ በተለይ ጠንካራ የፓርቲ ተቋም ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትን በዘላቂነት ማስከበር፣ የልማትና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች እና ጠንካራ የተግባቦት ሥራዎች ናቸው ብለዋል።

በመድረኩ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ስለወቅታዊ የሕግ የበላይነት የማስከበር እንቅስቃሴ እና የተገኘውን ውጤት በተመለከተ ገለጻ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የተጀመረው ሕግን የማስከበር ሥራ ለአማራ ሕዝብ እፎይታን የሰጠና በተለያየ ወንጀል ውስጥ ተሰማርተው የነበሩ አካላትን ወደ ሕግ ያቀረበ ነው ብለዋል።

አቶ ደሳለኝ “አማራ ክልል ወደ ሕግ ማስከበር ሥራ መግባቱ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን ሴራ ያከሸፈ ነው” ያሉ ሲሆን ፥ የጠላት ህልም ክልሉን የትርምስ ቀጠና በማድረግ ሀገርና ሕዝብን ማዋረድና መበተን እንደነበርም አስገንዝበዋል።

ይሁን እንጅ በሕዝቡ ጥያቄ መሰረት በተወሰደ ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ የጠላት ተላላኪ ወንጀለኞችን ወደ ሕግ በማቅረብ የአማራን ሕዝብ ሰላም ያስከበረ ነውም ብለዋል በማብራሪያቸው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.