Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ከአሜሪካ ጋር አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ግንኙነት አላስፈላጊ ፉክክር እና እሰጥ-አገባ ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ አስታወቀች።

የቻይና የኮሙኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የውጭ ጉዳይ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ያንግ ጂቺ ÷ አሜሪካ በተለያዩ መንገዶች ቻይናን እየተጫነች መሆኑን ገልጸዋል።

ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የሁለቱን ሀገራት የትብብር እና የሁለትዮሽ ግንኙነት አጣብቂኝ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ያንግ ጂቺ ይህን ያሉት ለአሜሪካው ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ሲሆን ጉዳዩን ያስታወቁትም ሁለቱ ወገኖች ሉግዘምበርግ ባካሄዱት 5 ሠዓታት የፈጀ የሁለቱዮሽ ውይይት መሆኑን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ÷ አሜሪካ ከቻይና ጋር ምንም ዓይነት ፉክክር እና እሰጥ-አገባ ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ መግለጻቸውን ጂቺ አስታውሰዋል።

ከዚህ ባለፈም በቻይና የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ እንደማትገባ እንዲሁም የታይዋንን የራስ ገዝነት ጥያቄ እንደማይደግፉ በተደጋጋሚ መናገራቸውንም ነው ያስታወሱት።

ይህ የአሜሪካ አቋም በቻይና ዘንድ ትልቅ ሥፍራ እንዳለው እና እንደሚከበርም ነው ያንግ አስረግጠው የተናገሩት፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲቀጥል ÷ ፕሬዚዳንት ሺ ያቀረቡት በመከባበር ፣ በሠላም አብሮ በመኖር እና ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ መሥኮች ላይ በትብብር መሥራት ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ አዋጪ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የአሜሪካው ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን በበኩላቸው ÷ ሁለቱ ሀገራት ለግንኙነታቸው የማይጣሱ ገደቦችን ማበጀት እና መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

ከስብሰባው በኋላ ሁለቱ ወገኖች ውይይታቸው ፍሬያማ እና ጥልቅ እንደነበር አመላክተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.