Fana: At a Speed of Life!

በአሶሳ ከተማ የፈጠራና የምርምር ሲምፖዚዬም እየተካሄደ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤጄንሲ የተዘጋጀ የፈጠራና የምርምር ሲምፖዚዬም በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

“ፈጠራና ምርምር ለአገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው ሲምፖዚዬም÷ በክልሉ የአሶሳ ዞን ወረዳዎችና በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የፈጠራ ውጤታቸውን አቅርበዋል፡፡

በተማሪዎች የተዘጋጁ ለወርቅ ማውጫ የሚያገለግል የድንጋይና አፈር መፍጫ፣ የውኃ መሳቢያ፣ ኢንኩቤተር፣ ማይክሮስኮፕ፣ ቬንቲሌተር፣ መሰንጠቂያ ማሽን፣ የምግብ ማብሰያ፣ ተሽከርካሪዎች፣ የተለያዩ ሶፍትዌሮችና ሌሎች የፈጠራ ውጤቶች በሲምፖዚዬሙ ቀርበዋል፡፡

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ኃይሉ ሲምፖዚዬሙ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱን ጠቁመው÷ ዓላማውም የፈጠራና የምርምር ባለቤቶችን ከማበረታታት ባሻገር ለአገርና ለክልሉ ጠቀሜታ ያላቸውን የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ማጎልበት ነው ብለዋል፡፡

ጅምር የፈጠራ ውጤቶችን ያቀረቡ የፈጠራ ባለቤቶች በቀጣይ ከዚህ የተሻሉ ሥራዎችን ይዘው ለመቅረብ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡

ኤጀንሲው በዘርፉ ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን ከምርምር እና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ÷በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አሠራሮችን ለማዘመንና የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ጃፈር ሀሩን በበኩላቸው÷ ተማሪዎች ያቀረቧቸው የፈጠራ ሥራዎች አበረታችና የበለጠ ሊዳብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ቢሮው የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች በግብዓት፣ በገንዘብና በቴክኒክ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የፈጠራ ውጤቶቻቸውን በሲምፖዚዬሙ ላይ ያቀረቡ ተማሪዎችም በአካባቢያቸው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በግብዓትነት መጠቀማቸውን ጠቁመው÷ የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ቢደረግላቸው የተሻለ መሥራት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

በሲምፖዚዬሙ ላይ የፈጠራ ሥራ ላቀረቡ ተሳታፊዎች ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን÷ ውድድሩን ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት ላሸነፉ የፈጠራ ባለቤቶች የማበረታቻ ገንዘብ የተበረከተላቸው መሆኑንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.