Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በሴቬሮዶኔስክ ከተማ የመሸጉ የዩክሬን ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ ጠየቀች 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በሴቬሮዶኔስክ ከተማ በተለይም በኬሚካል ፋብሪካ ውስጥ የመሸጉ የዩክሬን ወታደሮች ትጥቃቸውን እንዲያወርዱና እጅ እንዲሰጡ ጠየቀች፡፡

የከፋ ደም- አፋሳሽ በተባለው የሴቬሮዶኔስክ  ውጊያ የሩሲያ ወታደራዊ ኃይሎች አብዛኛው የዩክሬን ጦር ከምሥራቃዊቷ የኢንዱስትሪ ከተማ ሴቬሮዶኔስክ እንዲወጣ ያደረጉ ሲሆን፥  ነገር ግን ከተማዋን ሙሉ በሙሉ እንዳልተቆጣጠሩ ተዘግቧል፡፡

በመሆኑም የዩክሬን ተዋጊ ኃይሎች በሴቬሮዶኔስክ ከተማ  በሚገኘው የኬሚካል ፋብሪካ ውስጥ በመመሸግ የሩሲያን ጦር እየተከላከሉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የሩሲያ ብሔራዊ የመከላከያ አስተዳደር ማዕከል ኃላፊ ሚኻኤል ሚዚንሴቭ ከኢንተርፋክስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ የዩክሬን ወታደሮች የሚያደርጉትን “ትርጉም-የለሽ”  የመከላክል ሙከራ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዩክሬን “ከ500 በላይ ንፁሀን ዜጎች ከወታደሮቹ ጋር ታግተውብኛል” በሚል ላቀረበችው ክስ  የማዕከሉ ኃላፊ በሰጡት ምላሽ፥ ንፁሃን ዜጎችን ለማስወጣት የመውጫ በር እንደሚከፈትላቸው ነው ያስታወቁት፡፡

የሉሃንስክ ክልል አስተዳዳሪ ሰርሂ ጋይዳይ በአዞት የኬሚካል ፋብካ ውስጥ ከወታደሮቹ ጋር የታገቱት ንፁሃን ዜጎች “ሊቋቋሙት በማይችሉት የሥነ ልቡና ጫና ውስጥ ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ አስተዳዳሪ አክለውም፥  “የእኛ ኃይሎች በሦስት አቅጣጫ ተሰልፈው በመከላከል ጠላት ወደ ሊቻንስክ እንዳይገባ በማድረግ ላይ ናቸው” ነው ያሉት፡፡

ይሁን እንጅ  ዩክሬን  የሰብዓዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የምታቀርበው ክስ ወታደሮቿን ከአዞት ፋብሪካ ውስጥ ለማሰወጣት በማሰብ  ሊሆን እንደሚችል  የሩሲያ ጦር ገልጿል፡፡

የከተማዋ ከንቲባ ኦሌክሳንድር ስትሪዩክ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ሩስያ የሰጠችው የማስጠንቀቂያ ቀነ ገደብ በማለቁ፥ ከተማዋን ከየአቅጣጫው እያጠቁ መሆኑንና የዩክሬን ኃይልም እስካሁን እጅ አለመስጠቱን ተናግረዋል።

የዩክሬን ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ ወይንም ከከተማዋ ጠቅለው እንዲወጡ ከሩስያ በኩል የቀረበላቸውን ጥሪ ለመቀበል እስካሁን ፈቃደኞች አልሆኑም።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰሜን አትላንቲክ አገሮች የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የመከላከያ ሚኒስትሮች ተጨማሪ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን በመላክ የተዳከመውን የአገሪቱን የጦር መጋዘን ለማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በብራስልስ ተሰባስበው  እየመከሩ ይገኛሉ።

ይህም ጦርነቱ እንዲቀጥል፥ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰትና የፈጠረው ዓለማቀፋዊ ችግር እንዲባባስ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም የሚል ትችት ነው እየቀረበበት ያለው።

ፕሬዚዳንት ዘለልስኪ በበኩላቸው፥ “ጠንካራ የመከላከል ውጊያ ማድረጋችንን መቀጠል አለብን፥ ጠላት እየደረሰበት ካለው የጉዳት መጠን አንፃር ወደፊት የመግፋት አቅሙ ይዳከማል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከ100 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የሚኖሩባት የሴቬሮዶኔስክ ከተማ፥ ሩሲያ በምታካሂደው የምስራቃዊ ዩክሬን ውጊያ ዋነኛ የጦር ዒላማ ስለመሆኗም ተነግሯል፡፡

ኪየቭ በውጊያው በየቀኑ ከ100 እስከ 200 ወታደሮቿ እንደሚገደሉ እና በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ እንደሚቆስሉባት የገለፀች ሲሆን፥ ሴቬሮ ዶኔስክን ከሊቻነስክ የሚያገናኘው ድልድይ መፍረሱን ተከትሎ ንፁሃን ዜጎችን ጨምሮ የዩክሬን ተከላካይ ኃይሎች ከበባ ውስጥ ስለመሆናቸው ሮይተረስ እና አር ቲ ዘግበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.