Fana: At a Speed of Life!

የጋዜጠኝነት እና የማህበረሰብ አንቂነት የሚና መደበላለቅ ድንበር ሊበጅለትና በሕግ ሊመራ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋዜጠኝነት ሙያ እና ማህበረሰብን የማንቃት እንቅስቃሴ የሚና መደበላለቅ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ድንበር ሊበጅለትና በሕግ ሊመራ ይገባል ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

የሚዲያ ልማት ባለሙያው አቶ ሄኖክ ሰማእግዜር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ የየራሳቸው ሙያዊ ሥነ ምግባርና መርሆ ያላቸው ጋዜጠኝነት እና የማህበረሰብ አንቂነት በመርህ ሊመሩና በአግባቡ ስራ ላይ ሊውሉ ይገባል፡፡

ትክክለኛነት፤ ገለልተኛነት እና ሚዛናዊነት የመሳሰሉ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ መረጃ የመስጠት፣ የማስተማርና የማዝናናት ተልዕኮን የመወጣት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተጣለ ግዴታ እንደመሆኑ ባለሙያው ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

በአንጻሩ በማህበረሰቡ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ለማስቻል በሚደረግ ሂደት ደግሞ የአንቂነት ወይም የወትዋችነት (አክቲቪዝም) እንቅስቃሴ የሚመራበት ራሱን የቻለ መርሆም መንገድም እንዳለው ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡ ጋዜጠኝነትም ሆነ ማህበራዊ አንቂነት ሁለቱም ከመርህ እና ከሕግ ውጭ ሊሰሩና ሊሆኑ እንደማይችሉ በመጠቆም።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ዮሐንስ ሽፈራዉ በበኩላቸው÷ በአንጻራዊነት የማህበራዊ እና የመደበኛ መገናኛ ብዙሃን መስፋፋትን ተከትሎ የሁለቱም የየቅል የሆኑ የስራ መስኮች የሙያ መደበላለቅ በመፍጠራቸው አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው ብለዋል፡፡

የሙያን መርሆ አለማክበር እና ፓለቲካዊ ውግንናን የመሰሉ ግላዊ ፍላጎቶች የሚና መደበላለቁ እንዲፈጠር ማድረጉን እንደ አንድ ማሳያ ምክንያት ያነሳሉ ባለሙያዎቹ ፡፡

የመስኮቹ የሚና መደበላለቅ በሀገርና ሕዝብ አንድነት ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለማስቀረት ደግሞ የአቅም ግንባታና የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ነው ዶክተር ዮሐንስና አቶ ሄኖክ የገለጹት፡፡

በተለይም የማህበረሰብ አንቂነት ሥነ ምግባርን በተከተለ መንገድ እንዲሰራ እና ውጤት እንዲኖረው ሙያዊ እገዛ ማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ጋዜጠኝነትም ሆነ የማህበረሰብ አንቂነት ሙያዊ ሥነ ምግባር ጠብቆ እና ሕግ አከብሮ እንዲሰራ መንግስት፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እና ሌሎች አካላት ኃላፊነታቸውን በሚጠበቀው ደረጃ ልክ መወጣት እንዳለባቸው ነው ባለሙያዎቹ የጠቆሙት፡፡

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.