Fana: At a Speed of Life!

የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ባለፉት ሰባት ወራት ለ1 ነጥብ 67 ሚሊዮን ዜጎች ስራ መፈጠሩን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገር አቀፍ ደረጃ የስራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴ በተቀናጀ መንገድ በውጤት ተኮር ስርዓት መመራት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

የስራ ዕድል ፈጠራ ብሄራዊ ምክር ቤት የሰባት ወራት ስራ አፈጻጸም ዙሪያ በሻራተን አዲስ ሆቴል ውይይት ተደርጓል።

በሃገር አቀፍ ደረጃ የስራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴ በተቀናጀ መንገድ በውጤት ተኮር ስርዓት መመራት አለበት  ብለዋል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ከዕቅድ ጀምሮ ከክልሎች ጋር በመናበብ የተሻለ ዝግጅት መደረጉን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዕቅዱ ግማሽ ዓመት በተደረገው ቅንጅታዊ ርብርብ ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል።

በመድረኩ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ባለፉት ሰባት ወራት ለ1 ነጥብ 67 ሚሊዮን ዜጎች ስራ መፈጠሩ ተገልጿል።

በየደረጃው የስራ አመራሩ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉ ለውጤቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደነበረው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አመልክተዋል።

የፌዴራል ስራ ፈጠራ ኮሚሽን ያጠናከረው የአፈፃፀም ሪፖርት ”ለእውነት የተጠጋ” መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል።

ወጣቱን የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በማድረግ የቤተሰብ ቢዝነስ የማቋቋም የስራ ባህል ለማዳበር በስፋት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የብሄራዊ ስራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.