Fana: At a Speed of Life!

የሀገራቱን ባሕል ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራት እንደምትፈልግ ደቡብ ሱዳን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ሱዳን የባሕል ፣ ሙዚየም እና የብሔራዊ ቅርስ ጥበቃ ሚኒስቴር ምክትል ጸሐፊ ኩዋክ ዌክ ዎል ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የሀገራቱን ባሕል ለማሳደግ በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጸሃፊው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የሁለቱን ሀገራት ባሕል እና ጥበብ ለማሳደግ የደቡብ ሱዳን የባሕል ፣ ሙዚየም እና የብሔራዊ ቅርስ ጥበቃ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረሙ ጠቁመዋል፡፡

ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምስራቅ አፍሪካ የኪነ-ጥበብ እና የባሕል ፌስቲቫል የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች ባሕላዊ እና ጥበባዊ ዕሴቶቻቸውን የሚያሳዩበት እንዲሁም ማኅበራዊ አኗኗራቸውን እና ፖለቲካዊ ምልከታቸውን የሚጋሩበትን ምኅዳር የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ያመቻቸ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኩዋክ ዌክ ዎል በአዲስ አበባ የተካሄደውን የምስራቅ አፍሪካ የኪነ-ጥበብ እና የባሕል ፌስቲቫሉን መከታተላቸውን ገልጸው፥ በተመለከቷቸው ባሕላዊ አለባበሶች፣ ጭፈራዎች፣ ቁሶች እና የየሀገራቱ የጥበብ ውጤቶች መደነቃቸውንም ነው ያወሱት፡፡

ደቡብ ሱዳንም ተመሳሳይ ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ዕቅድ እንዳላትና ኢትዮጵያ እንደምትካፈልበትም አስታውቀዋል፡፡

ሀገራቱ በየተራ በሚያዘጋጇቸው ፌስቲቫሎችም ህዝቦቻቸው ባሕላቸውንና አኗኗራቸውን በቀላሉ መለዋወጥ እንደሚችሉና ትሥሥር እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል፡፡

ኩዋክ ዌክ ዎል ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ታሪክ፣ ቋንቋ እና ባሕል ከመጋራታቸውም በላይ የአባይ ወንዝ ተጋሪ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቤቴ እንደሆነች ነው የሚሰማኝ ሲሉ የገለጹ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በሁለት ሀገር የሚኖሩ አንድ ህዝቦች ናቸው ሲሉ ነው ሀገራቱ በበርካታ ዘርፎች መጋመዳቸውን እና የማይነጣጠሉ ህዝቦች መሆናቸውን ያወሱት፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.