Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች- አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላትን ግንኙነትና ትብብር ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምሥራቅ እና የደቡባዊ አፍሪካ አገራት ዳይሬክቶሬት ጀኔራል አምባሳደር ኤሊፍ ኮሞሎኡ የን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም መንግስት ለሰላም እያደረገ ያለውን ጥረትና ፍላጎት አብራርተዋል።

በግጭቱ ምክንያት ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይከሰት፣መንግስት የምግብ አቅርቦት እና ድጋፍ እንዲኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን እና ከዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዲሁም ለጋሽ አካላት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግስት ለስራው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልፀዋል።

መንግሥት ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት ለሰላም እና መረጋጋት ባለው ፅኑ ፍላጎት በአሁኑ ወቅት ተስፋ ሰጭ ጅምሮች መኖራቸውን ገልፀው÷ ይሁን እንጂ ህወሓት በየጊዜው የሚያሳየው ተለዋጭ የሆነ አቋም የሰላም ጥረቱን ወደ ኋላ እየጎተተው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ አማካይነት ለሰላም የሚያደርጉትን ጥረት እና ተነሳሽነት አሁንም መቀጠሉን ገልፀዋል።

አምባሳደር ኤሊፍ ኮሞሎኡ የን በበኩላቸው ቱርክ ሀቀኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆኗን ገልፀው÷ ግንኙነቱ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል። በትብብር መስኮች በወታደራዊ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሰላም ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት ማድነቃቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.