የግብርና ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የ2014/2015 ምርት ዘመን የባለድርሻ አካላት የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እያካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት እንደተገለጸውም÷ በክልሉ በ2014/2015 የመኸር ወቅት ከ14 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ ክልሉ ካለው ምቹ ስነ ምህዳር አንጻር በ2013/14 የምርት ዘመን የተገኘው አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አፈጻጸሙን ለማሻሻልም በአንዳንድ ዞኖች የተጀመሩ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ በሌሎችም ዞኖች እንዲሰፋ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው÷ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራዎችን በመተግበር የክልሉን የመልማት አቅም አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የግብርና ሥራዎችን በማዘመን እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
በ2014/2015 የመኸር ወቅት ከ350 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት በማልማት÷ ከ14 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ መያዙን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!