Fana: At a Speed of Life!

በጣሊያን በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር 197 ደርሷል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣሊያን በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር 197 መድረሱን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 4 ሺህ 600 መድረሱንም ነው ያስታወቁት።

በአንድ ቀን ብቻ 49 ሰዎች መሞታቸውንም ገልጸዋል፤ ይህም ቫይረሱ በሃገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

በቫይረሱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከቻይና ቀጥሎ ከየትኛውም ሃገር በላይ መሆኑም ተገልጿል።

የሃገሪቱ ብሄራዊ የጤና ኢንስቲትዩት እንዳለው የሟቾቹ አማካይ እድሜ 81 ሲሆን፥ ከሟቾቹ ውስጥ 72 በመቶዎቹ ወንዶች ናቸው።

በሃገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት ውስጥም 4 ነጥብ 25 በመቶዎቹ ለህልፈት እንደሚዳረጉም የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል።

ይህም ዓለም ላይ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑ ነው የተገለጸው።

የሃገሪቱ መንግስት የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሚል ትምህርት ቤቶችን እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መዝጋቱ ይታወሳል።

ከዚህ ባለፈም አንዳንድ የሃገር ውስጥ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝመዋል።

በሌላ በኩል በቫይረሱ በደቡብ ኮሪያ 6 ሺህ 767 ሰዎች ሰዎች ሲያዙ 46ቱ ለህልፈት ተዳርገዋል ነው የተባለው።

በተጨማሪም በኢራን 3 ሺህ 500 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን፥ 124 ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፥ ሃገራት በቻሉት መጠን የመከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.