Fana: At a Speed of Life!

ተቋማት ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች ቁፋሮ ሲያከናውኑ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመናበብ መስራት እንደሚገቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ለሚሰሯቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ቁፋሮ በሚያከናውኑበት ወቅት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመናበብ መስራት እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

በመዲናዋ በግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከመሬት በታች በተቀበሩ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የደቡብ እና ምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክቶች አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ አዲስ አበባ ዲስተሪክት ዳይሬክተር አቶ ጂሳ ካሳ÷ በበጀት ዓመቱ በቃሊቲና በለቡ አደባባይ አካባቢ በመሬት ውስጥ በተቀበሩ የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮች ላይ በመንገድ ስራ ምክንያት አደጋ መድረሱን ጠቅሰው በዚህም ከ11 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 4 ሺህ 500 ሜትር የኤሌክትሪክ ገመድ ወድሟል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት 10 በመሬት ላይ የተቀበሩ ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን በዲስትሪክቱ የዲስትሪቢውሽን፣ ኮንስትራክሽንና ሚይንቴናንስ ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ሀሺም ገልፀዋል፡፡

ቴሌ ጋራጅ፣ ሜክሲኮ ቡናና ሻይ፣ አየር ጤና አደባባይ፣ አፍሪካ ህብረት አደባባይ እና ካዛንችስ ሀናን ዳቦ ቤት አካባቢዎች ጉዳቱ ከደረሰባቸው መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን ጉዳቱ የደረሰው በአዲስ አበባ መንገድ ስራዎች፣ በኢትዮ ቴሌኮም እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ የህንፃ ግንባታ መሆኑን አቶ አህመድ አስታውቀዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ በእነዚህ አካባቢዎች በደረሰው ጉዳት ተቋሙ 11 ሚሊየን 920 ሸህ 249 ብር ያጣ መሆኑን አቶ አህመድ ጠቅሰው የደረሰውን ኪሳራ ተቋማቱ በህግ አግባብ እንዲከፍሉ ይደረጋል ማለታቸውን ከኢትየጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአጠቃላይም በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ለሚሰሯቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ቁፋሮ በሚያከናውኑበት ወቅት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመናበብ መስራት እንደሚገባ አቶ አህመድ አሳስበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.