Fana: At a Speed of Life!

በሀገራዊ ምክክሩ ህብረተሰቡ የመወያያ ሀሳቦችን በነጻነት እንዲያፈልቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገራዊ ምክክሩ ህብረተሰቡ ራሱ የመወያያ ሀሳቦችን በነጻነት እንዲያፈልቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትና ከባለድርሻ አካት ጋር ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተወያይቷል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ ”ሀገራዊ ምክክሩን አካታች ማድረግ ወሳኝ ” መሆኑን ገልጸው፥ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከክልሎች ጋር የትውውቅ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት÷ ክልሎች የእውቀት፣የሀሳብ፣ የበጀት እና ሌሎችንም ሁለንተናዊ ድጋፎች እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽነር መላኩ ገብረማርያም በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክር አድርገው ሳይሳካላቸው የቀሩ ሀገራት ዋነኛ ችግራቸው ለውይይት አጀንዳ ተቀርጾ ለህብረተሰቡ በመሰጠቱ እንደሆነ ጠቁመው÷ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክሩ መሰል ችግር እንዳያጋጥመው ህብረተሰቡ ራሱ የመወያያ ሀሳቦችን በነጻነት እንዲያፈልቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየወረዳው ያለውን ህብረተሰብ በምክክሩ ለማካተት እንደሚሰራ ጠቁመው÷ በቅርቡ የምክክሩን ጉዳይ የሚከታተሉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች በየክልሉ ይመደባሉም ነው ያሉት፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፥ ኮሚሽኑ የያዘው ዓላማ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን የጋራ አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው÷ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባት የማምጣት አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስትም ሁለንተናዊ ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ገንቢ ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ እና ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤት የጋራ ተጠቃሚነትን ማስቀደም እንደሚገባም ነው የተጠቆመው።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.