Fana: At a Speed of Life!

በምርጫ ወቅት የሚነሱ አለመግባባቶችን መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ያተኮረ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምርጫ ወቅት የሚነሱ አለመግባባቶችና ክርክሮች አፈታትን በማስመልከት አውደ ጥናት እያካሄዱ ነው፡፡

አውደ ጥናቱ በመጪው ነሃሴ ወር በሚከናወነው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸውን ሚና እና የህግ ማዕቀፎችን ማስተዋወቅ እንዲሁም ከዳኞች ጋር ምክክር ማካሄድ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ በምርጫ ሂደት ወቅት ለሚኖሩ የፍትህ ሂደቶች ልዩ የምርጫ ችሎት ማደራጀት ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከድምጽ ቆጠራ እና ከየምርጫ ውጤት ጋር ለተገናኙ ክርክሮች የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፥ ውሳኔው ፍትሃዊ እንዲሆንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በበኩላቸው፥ ፍርድ ቤቶች በገለልተኝነት ምርጫን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የማየት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ቦርዱ በፍድር ቤቶች የሚከናወኑ መሰል ጥረቶችን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በአውደ ጥናቱ በምርጫ ሂደት የሚከሰቱ አለመግባባቶች እና ክርክሮችን በመፍታት ሂደት፣ የጊዜ ሰሌዳ፣ የሚመለከታቸው አካላት ስልጣን እና አቤቱታ አፈታት ዙሪያ አዋጅ 1162/2011 በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ውይይት ይካሄዳል።

ከዚህ ባለፈም የምርጫ ክርክር ሂደት እና ህጋዊ ማእቀፉ እና የመረጃ ልውውጥ አስፈላጊነት በሚሉ ጉዳች ዙሪያ ምክክር የሚደረግ መሆኑን ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካና ከኬንያ የምርጫ ክርክር ሂደቶች ተሞክሮዎችን መጋራት እንዲሁም በምርጫ ጉዳዮች ላይ የተፋጠኑ ውሳኔዎችን ለመስጠት በሚያስፈልጉ ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት ይካሄዳል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.