Fana: At a Speed of Life!

እናቶቻችንና እህቶቻችን ደጀን ሆነው ሳይደግፉት የተገኘ አንድም ኢትዮጵያዊ ድል የለም-ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በነገው ዕለት የሚከበረውን የሴቶች ቀን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

እንኳን ለማርች 8 የሴቶች በዓል አደረሳችሁ!

የሴቶችን በዓል የምናከብረው የሁላችን በዓል ስለሆነ ነው፡፡ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን የቆምነው እናቶቻችን በከፈሉት ዋጋ በመሆኑ በዓሉ ልዩ ይሆንብናል፡፡ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር ናት ስንል አሳፍረው የሚያስከብሯት እናቶችና እኅቶች ነበሯት፤ አሏት ማለታችን ነው፡፡

ኢትዮጵያ በነጻነት ጸንታ እንድትኖር እናቶቻችንና እኅቶቻችን በአራት ዐውደ ግንባር ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ጀግና ፈጥረዋል፤ ለጀግና የሚሆነውን ስንቅ አዘጋጅተዋል፡፡ ጀግኖችን ተንከባክበዋል፡፡ እነርሱ ራሳቸውም በጀግንነት ተዋግተው ድል አድርገዋል፡፡ ለልጆቻቸው የጀግንነት ታሪክ እየነገሩ፣ ለሀገር መሠዋት ያለውን ክብር እያስተማሩ፤ እንዳይፈሩ እያደፋፈሩ፤ ጀግኖችንም እያሞገሡ፣ ለዚህች ሀገር ጀግና የፈጠሩላት እናቶቻችንና እኅቶቻችን ናቸው፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ሰው አድርጎ ፈጠረ፡፡ እናቶቻችንና እኅቶቻችን ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ጀግና አድርገው ፈጠሯቸው፡፡

እናቶቻችንና እኅቶቻችን ስንቅና ትጥቅ አዘጋጅተው ጀግኖችን ያዘምታሉ፡፡ ከዚያም አልፈው ራሳቸውም በጦር ሜዳ ደጀን ሆነው ስንቅና ትጥቅ ያዘጋጃሉ፡፡ እናቶቻችንና እኅቶቻችን ደጀን ሆነው ሳይደግፉት የተገኘ አንድም ኢትዮጵያዊ ድል የለም፡፡ ለተዋጊ ሠራዊት ስንቅና ትጥቅ ከማዘጋጀት አልፈው ቁስለኛውን ያክማሉ፤ ይከባከባሉ፡፡ የሞቱትን ይቀብራሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ መሣሪያ ነጥቀው፣ ጦር ታጥቀው፣ ወገባቸውን አሥረው በዐውደ ውጊያው ይገኛሉ፡፡ መርተው ያዘምታሉ፤ ተዋግተው ያሸንፋሉ፡፡

እነዚህ እናቶችና እኅቶች ዛሬም አሉ፡፡ የዚህች ሀገር ልዩ ጸጋዎች ናቸው፡፡ እነዚህ እናቶችና እኅቶች እስካሉ ድረስ ሀገር ጀግኖች ትወልዳለች፡፡ በሁሉም መስክ፣ በየትኛውም ቦታ፣ በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ፣ በምንም ዓይነት አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያን ክብር ያስጠብቃሉ፡፡ እናቶቻቸው ከራሳቸው ይልቅ ለልጆቻቸው ሲያደሉ አይተዋል፡፡ ልጆቻቸውም ከራሳቸው በላይ ለሀገራቸው ያደላሉ፡፡ ጦርነት ከማንም በላይ ሴቶችን እንደሚጎዳ እናቶቻችንና እኅቶቻችን ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም ምንጊዜም ለሰላም፣ ለይቅርታና ለፍቅርና ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ከዚያ አልፎ የሚመጣ ካጋጠማቸው ግን ‹እዚያው ውጊያው ላይ እንገናኝ› ይሉታል፡፡

እናቶቻችን በአራት ዐውደ ግንባር ዘምተው ያስከበሯት ሀገር፣ አራቱን ጠላቶቿን (ድህነትን፣ ኋላ ቀርነትን፣ መለያትንና ግጭትን) ድል አድርጋ በክብር እንድትኖር እንደሚያደርጓት እምነቴ ነው፡፡ ማርች ስምንትን ስናከብር ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ ተከብሮ፣ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ፣ በክብርና በነጻነት እንድትኖር ለማድረግ እናቶቻችንና እኅቶቻችን እንደገና የሚነሡበት ቀን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ክብር በሁሉም መስክ ተሠማርተው የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉዓላዊነት ሲያስጠብቁ ለነበሩ እናቶችና እኅቶች ይሁን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.