Fana: At a Speed of Life!

ከ156 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ156 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
 
ኮሚሽኑ በአንድ ሳምንት ውስጥ በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ባደረገው ክትትል ነው 60 ነጥብ 4 ሚሊየን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 96 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎችን የያዘው፡፡
 
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት አቃቂ ቃሊቲ ፣ ጅግጅጋ ፣ እና ድሬድዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ÷ በቅደም ተከተላቸው 18 ነጥብ 5 ሚሊየን ፣ 14 ነጥብ 2 እና 6ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዛቸው ተመላክቷል፡፡
 
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች እንደሚገኙበትም ተገልጿል፡፡
 
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን÷ ኮንትሮባንድ ሲያዘዋውሩ የተገኙ 8 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.