Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በቤልጂየምና ኔዘርላንድስ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አመራሮች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትህ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በብራስልስና በአካባቢው ከሚኖሩ የዳያስፖራ አመራሮችና የአውሮፓ ዲፌንድ ኢትዮጵያ አስተባባሪዎች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡

ሚኒስትሩ አራት አባላት ያሉትን የልዑካን ቡድን በመምራት በብራስልስ የሚገኙ ሲሆን ፥ በብራስልስና በአካባቢው ከሚኖሩ የዳያስፖራ አመራሮችና አስተባባሪዎች ጋር በአካል፣ እንዲሁም በኔዘርላንድስ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላትና በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ከሚገኙ የዲፌንድ ኢትዮጵያ አስተባባሪዎች ጋር በበይነ መረብ መክረዋል፡፡

ሚኒስትሩ በውይይቱ መግቢያ ላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ አገሮች በሚኖረው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችንና ድጋፎችን በተለይም በኮቪድ-19 መከላከል፣ ለመከላከያ ሠራዊትና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተደረገውን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ፣ እንዲሁም በ’’በቃ’’ እንቅስቃሴ፣ በታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤትና በዒድ እስከ ዒድ መርሐ ግብር የተደረጉ የማሳወቅና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን በመዘርዘር አመስግነዋል፡፡

በውይይቱ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴና በሂደቱ የዜጎችን መብት ስለማስከበር፣ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሰዎች አያያዝን በተመለከተ በአቃቤ ሕግና እና በፖሊስ መካከል ሚዛናዊ መስተጋብር ስለማስፈን፣ የተዛባ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ፈር ለማስያዝ ምን እየተደረገ እንደሆነ፣ በፍትህ ዘርፍ የሚካሄደው የሪፎርም ፕሮግራም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያዎችን የሰጡ ሲሆን፥ የዳያስፖራ ማኅበረሰቡን ተሳትፎ አድንቀው፥ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ብራስልስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.