Fana: At a Speed of Life!

በንጹሃን ላይ የሚፈጸም ግድያ የተሸናፊዎች ድርጊት ነው – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰሞኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በንጹሃን ላይ የተፈጸመው ግድያ የተሸናፊዎች ድርጊት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
 
በኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ÷በፌዴራልና በክልል መንግሥት እየተወሰደ ባለው ኦፕሬሽን አሸባሪ ቡድኖች ጥቃቱን መቋቋም ተስኗቸው ተበታትነዋል ብለዋል።
 
ይሁን እንጅ እነዚህ ተሸናፊ ኃይሎች ሽንፈታቸውን ላለመቀበል የፈሪ ዱላቸውን በንጹሃን ላይ አሳርፈዋል ነው ያሉት።
 
ይህን እኩይ ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎችን በዘላቂነት ማጥፋት የምንችለው በጋራ ስንቆም ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ÷በዚህ የፈሪ የሽብር ድርጊት ሳንደናገጥ ተባብረን መቆም አለብን ብለዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ኢትዮጵያ በየትኛውም ፈተና ውስጥ አልፋ እንደ አገር ጸንታ ትቆማለች ሲሉም ገልጸዋል፡፡
 
የስኬት መንገድ በፈተና የተሞላ መሆኑን በመገንዘብ ማንኛውንም ዋጋና መስዋዕትነት ከፍለን የኢትዮጵያን ሰላም እናረጋግጣለን ማለታቸውንም ዋልታ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.