Fana: At a Speed of Life!

ጣልያን በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምትደግፍ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጣልያን የታችኛው ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት የአውሮፓ ጉዳዮች ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፒየሮ ፋሲኖ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን ጣልያን እንደምትደግፍ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያና በጣልያን የፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴዎች መካከል የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተዘጋጀው የምክክር መርሐ ግብር÷ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይና የሰላም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ከጣልያን የታችኛው ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የአውሮፓ ጉዳዮች ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፒየሮ ፋሲኖ ጋር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረውን የሃገራቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ዶክተር ዲማ ነገዎ በውይይቱ ወቅት÷ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
በዚህም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም በአገሪቱ አካታች ውይይት እንዲካሄድ በብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚከናወኑ ተግባራትን በማስተባበር ረገድ የተሰሩ ስራዎችን አብራርተዋል።
የጣልያን የታችኛው ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የአውሮፓ ጉዳዮች ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፒየሮ ፋሲኖ በበኩላቸው÷ በመንግስት በኩል በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራት አድንቀዋል፡፡
ጣልያንም ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን ትደግፋለች ማለታቸውን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይም የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.