Fana: At a Speed of Life!

ማህበራዊ ብዝሀነት ያለው የደቡብ ኦሞ ዞን መደመርን ያሳያል -ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣የካቲት 29፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
 
በውይይቱ ወቅት ከነዋሪዎች አንደበት የሚያስፈልጋቸውን ማወቃቸውን ገልፀዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ የአርብቶ አደር ፓሊሲ ለጉዳዮቹ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን በመግለፅ አካታች ልማትን ለመተግበር መንግስት ቁርጠኛ እንደሆነ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከነዋሪዎች ለተነሱ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንዳሉት ህብረተሰቡ በየጊዜው የሚያነሳቸውን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ለመመለስ የመንግሥትን አቅም ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
 
ከጂንካ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ማሟላት ጋር በተያያዘ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እንዲሟላ ይደረጋል ብለዋል፡፡
 
ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ለተነሱት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው እንደጠቆሙት የክልል የዞን እና የወረዳ መዋቅር በሰፋ ቁጥር የሚጨመር ተጨማሪ በጀት የማይኖሮ በመሆኑ ጥቅምና ጉዳቱን መለየት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
 
በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ክልል በአንድ ብሄር ብቻ የታጠረ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል የተመሰረቱትም ክልሎች በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን አቅፈው መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡
 
በቀጣይ በጥናትና በውይይት የሚመጣውን አማራጭ በማየት ውጤቱን ወደ ፊት የምናይ ይሆናል ማለታቸውን ከደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጂንካ ከተማ ሲገቡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ርስቱ ይርዳውና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
 
የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ፣የክልልና ሌሎች የፌዴራል የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.