Fana: At a Speed of Life!

“ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ ለሰላም ደግሞ ሁሉም ሰው መሰረት ነው” – አቶ ብናልፍ አንዱአለም

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ ለሰላም ደግሞ ሁሉም ሰው መሰረት ነው” ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ተናገሩ፡፡

“ሃይማኖት ለሰላም” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በጉባዔው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና የመንግስት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ ለሰላም ደግሞ ሁሉም ሰው መሰረት ነው ብለዋል፡፡

ሰው ከፈጣሪው ጋር ከተስማማ ከራሱ ጋር ይስማማል፤ ከራሱ ጋር ከተስማማ ደግሞ ከሌላው ጋር መስማማት ይችላል ነው ያሉት አቶ ብናልፍ፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ በውስጣቸው ሰላምና ፍቅርን የያዙ ስለመሆናቸውም÷ “ወንዞች፣ ሀይቆች፣ ኩሬዎች እና ምንጮች ስማቸው ቢለያይም÷ ሁሉም በውስጣቸው ውኃ ይዘዋል፤ ሃይማኖቶችም ቢለያዩም በውስጣቸው ሰላምና ፍቅርን ይዘዋል” ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው÷ የክርስትናም ይሁን የእስልምና አስተምህሮት “ስለሰው ልጆች ሰላምና ፍቅር” ነው ብለዋል።

ይሁን እና አንዳንዶች የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ተሸሽገው የሃይማኖቶች እሴት ያልሆነውን ተግባር እንደሚፈጽሙ ጠቁመው÷ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የገቡ ኃይሎች እጃቸውን ሊያነሱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር እና በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው ጉባዔ ሃይማኖት ለሰላም፣ ለወንድማማችነትና ለአብሮነት መሰረት መሆኑ ተገልጿል፡፡

“ሃይማኖትና ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሁም የሃይማኖትና መንግስት ግንኙነት እና ትብብር “ የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ለውይይት ቀርቧል።

በታሪኩ ለገሰ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.