Fana: At a Speed of Life!

ከድህነት ወለል በታች የሆኑ የከተማ ነዋሪዎችን ችግር ለማቃለል በ83 ከተሞች የሴፍትኔት መርሃ ግብር እንዲካሄድ ከስምምነት ተደረሰ

አዲ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በ11 ከተሞች ሲተገበር የቆየው የከተሞች ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በ83 ከተሞች ላይ እንዲሰፋ ከስምምነት ላይ መደረሱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በከተማና መሰረተልማት ሚኒስቴር የከተሞች ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት በከተሞች ምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ እየመከረ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀንን ጨምሮ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዘርፉ የክልልና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ከተሞች ለአገር እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፥ በአገራችን ፈጣን የሆነ የክትመት ምጣኔ እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ በየዓመቱ 5 ነጥብ 4 በመቶ ክትመት እንደሚመዘገብ ጠቅሰው፥ የብዙ አገራት የዕድገት መለኪያ የክትመት ምጣኔ በመሆኑ የአገራችን ከተሞች የክትመት ምጣኔ የዜጎችን ህይወት በሚለውጥ መልኩ ሊመራ ይገባል ብለዋል፡፡

ከተሞች በአንድ ቦታ በርካታ ሕዝብ ተጠጋግቶ የሚኖርባቸው የአንድ አገር የእድገት ምሰሶዎች ቢሆኑም፥ ከድህነት ወለል በታች የሆኑ በርካታ ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም÷ በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የከተሞች ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተቀርጾ ወደትግበራ ተገብቶ በ11 ከተሞች ሲተገበር መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ከዓለም ባንክ ጋር በተገባው ውል መሰረትም በመርሃ ግብሩ የተሻለ አፈጻጸም በመመዝገቡ 72 ከተሞችን በመጨመር በድምሩ በ83 ከተሞች ላይ ስራውን ለማስፋት ስምምነት ላይ ተደርሷል ማለታቸውን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የሁለተኛው ምዕራፍ የከተሞች ሴፍቲኔትና ስራ መርሃ ግብር ከትግራይ ክልል ከተሞች ውጪ ባሉ 77 ከተሞች ላይ ትግበራ መጀመሩን ገልጸው÷ በዝግጅት ምዕራፍ ለአመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.