Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መሥራት ይገባል- የአውሮፓ ኅብረት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መስራት እንደሚገባ የአውሮፓ ኅብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺቺ ገለጹ።

ኮሚሽነሩ በሶማሌና ትግራይ ክልሎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በስፍራው በመገኘት ጎብኝተዋል።

የጉብኝታቸውን ማጠናቀቅ አስመልክቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ከጉብኝቱ በኋላ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንንና ከክልል የስራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው በተለይም የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ሂደት ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መሻሻሉን ጠቅሰው በቀጣይም እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል በነበራቸው ጉብኝትም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን አስታውሰው ድርቁ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን አንስተዋል።

በድርቁ ሳቢያ በተለይም ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸውን እንደተመለከቱ ጠቅሰው ከሚቀርበው የእለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ስራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

በመቐለ ከተማ ተገኝተውም ባካሄዱት የሁለተኛ ቀን ጉብኝት በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ምልከታ ማድረጋቸውን አውስተዋል።

በትግራይ ክልል ቆይታቸው የሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ሲገቡ መመልከታቸውን አስታውሰው የመንግስትን ጥረት በማድነቅ ሰብአዊ አቅርቦቱ መሻሻል እያሳየ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.