Fana: At a Speed of Life!

ሽብርተኛና ለሀገር ደኅንነት አደጋ በሆኑ ተላላኪ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በየትኛውም አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኛ እና የአገር ደኅንነት አደጋ የሆኑ ተላላኪ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እንደገለጹት÷ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ ቀደም ብሎ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አሸባሪዎችና የአገር ደኅንነት አደጋ የሆኑ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የተሳካ ሕግ የማስከበር እርምጃ ተወስዷል።

ሕግ የማስከበር እርምጃው ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው ለነበሩ የሰላምና ደኅንነት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጸው÷ የኢትዮጵያን ጠላት ተላላኪዎችን አቅም ያዳከመ መሆኑንም ነው የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ የተናገሩት፡፡

በየትኛውም አካባቢ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚፈፀም ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከዚህ አኳያ አሸባሪው ሸኔ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የፈፀመው ጥቃት የአገር ጠላት መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች በሚገኙ ሕገ ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪ ቡድን የማንንም ብሔር ወይም ሃይማኖት የማይወክል የአገርና ሕዝብ ጠላት በመሆኑ÷ በተባበረ ክንድ ልናጠፋው ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም ህብረሰተቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር የሚያደርገውን ትብብር በማጠናከር አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ላይ የሚፈፀሙ ዘግናኝ ድርጊቶችና የሽብር እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈልና የብልጽግና ጉዞውን ለማደናቀፍ ያለሙ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ አገር የማፈራረስ ህልማቸው ፈፅሞ ሊሳካ አይችልም ብለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በሕግ ማስከበሩ የላቀ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው÷ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአሸባሪው ሸኔ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች የፈፀማቸውን ጥቃቶች ተከትሎ በፀጥታ ኃይሉ በተወሰደው እርምጃ በርካቶች መደምሰሳቸውንና በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አመላክተዋል፡፡

በአገርና በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሰ ያለው ቡድን እስከመጨረሻው እስከሚወገድ የጸጥታ ኃይሉ ሕግ የማስከበር እርምጃ እንደሚቀጥል አረጋግጠው÷ ለዚህም መላው ሕዝብ በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.