Fana: At a Speed of Life!

የህወሃት ሽብር ቡድን የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ መከልከሉን መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሃት ሽብር ቡድን የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ መከልከሉን መንግስት ገለፀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ መንግስት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሷል።

ከተለያዩ አለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበርም አስፈላጊ መሰረታዊ ድጋፎች በየብስም በአየርም ሲያጓጉዝ መቆየቱንም ነው መግለጫው ያስታወቀው።

አሸባሪው ቡድን ይህንን የመንግስትን ጥረት ጥላሸት ለመቀባትና የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን ለመንዛት ሲል ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰብአዊ ድጋፎች የሚግቡበትን ሂደት ልማስተጓጎል በተደጋጋሚ መሞከሩን መንግስት ገልጿል።

በየብስ የሚገቡትን ሰብአዊ ድጋፎች ለትግራይ ህዝብ እንዳይደርሱ መንገድ በመዝጋትና የእርዳታ ማስተላልፊያ ኮሪደሮች አካባቢ ትንኮሳ በመፈጸም ከራሱ የፕሮፖጋንዳ ስሌት ባሻገር ለትግራይ ህዝብ ግድ እንደሌለው በተግባር እያሳየ መምጣቱንም ነው የጠቆመው።

በሽብር ቡድኑ በኩል የሚመጡ እንቅፋቶችን በመቋቋም መንግስት አስፈላጊውን ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረጉ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል ያለው መግለጫው፥

ሆኖም አሁን መንግስት ያመቻቸውና በየቀኑ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም የህጻናት አልሚ ምግቦች የሚላክበትን የአየር በረራ የሽብር ቡድኑ መከልከሉና ከትናንት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ ማድረጉ እንደታወቀም አመልክቷል።

መግለጫው ይህ የህወሃት የሽብር ቡድን እርምጃ ቡድኑ የትግራይን ህዝብ የሃሰት ፕሮፖጋንዳው መሳሪያ ከማድረግ ውጪ ሌላ አላማ እንደሌለው ዳግም በተግባር የሚያረጋግጥ ነው ብሏል።

ይህንን የሽብር ቡድኑን ውሳኔ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው የክልከላውንም ምክንያት እንዲያጣራ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም መንግስት እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ የትግራይ ክልል ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጠው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.