Fana: At a Speed of Life!

በጉራ ፈርዳ የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳት በሰው ሕይወት ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ 45 ተከሳሾች እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ 45 ተከሳሾች እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰኖባቸዋል።
የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሚዛን -ቦንጋ-ጋምቤላ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም “በወረዳው የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ምንም መሬት የላቸውም፤ መሬታችንን ለቀው መሄድ አለባቸው” በማለት በቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ የሚኖሩ የሸኮና የመዠንገር ብሔረሰቦች በአማራ ብሔር ላይ የጦር መሳሪያ አንስተው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ አድርገዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በጉራ ፈረዳ ወረዳ ጌኒቃ ቀበሌ ሌንጣ መንደር አንድ የሸኮ ብሔረሰብ ተወላጅ ተገድሎ በመገኘቱ ይህን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ገዳዩ ማን እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ “ልጃችንን የገደሉት አማራዎች ናቸው፤ የእኛ ሰው ሞቶ አማራ እዚህ ሀገር ቆሞ አይሄድም” በማለት ሌሎች የጦር መሳሪያ እንዲያነሱ ማድረጋቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
በዚህም የ30 ሰዎች ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እአንዲጠፋ፣ 14 ሰዎች የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ፤ 3 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት እንዲወድም እና 5 ሺህ 273 የሚሆኑ የአከባቢው ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርገዋል፡፡
በዚሁ መሰረትም፥ ተከሳሾች በህብረትና በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት የእርስ በርስ ጦርነት ማስነሳት ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሚዛን -ቦንጋ-ጋምቤላ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን ሲመለከተው ከቆየ በኋላ በ45 ተከሳሾች ላይ እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፎባቸዋል።
በዚህም መሰረት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሚዛን -ቦንጋ-ጋምቤላ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት በ45 ተከሳሾች ላይ የሚከተለውን የቅጣት ወሳኔ አስተላልፏል።
ኮንስታብል ኢሳቅ ጃፍሮ የተባለ ፖሊስን ጨምሮ ስምንት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ23 ዓመት ፅኑ እስራት፣ ሦስት ተከሳሾች በ18 ዓመት፣ አራት ተከሳሾች በ16 ዓመት ፣ አራት ተከሳሾች በ15 ዓመት ፣ ሰባት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ10 ዓመት ፅኑ እስራት አንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
ቀሪ አስራ ዘጠኝ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው ከ8 ዓመት ከ5 ወር እስከ 3 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.