Fana: At a Speed of Life!

ዲጂታላይዜሽን በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ተወዳዳሪ ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ ነው-ዶ/ር በከር ሻሌ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዲጂታላይዜሽን በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ተወዳዳሪ ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ ነው ሲል የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ዓመታዊ የሥራ አፈጻፀሙን ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን ገምግሟል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ ዲጂታላይዜሽን በቴክኒክና ሙያ የምርጫ ሳይሆን ተወዳዳሪ ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ በመሆኑ ከተቋማት ጀምሮ ያለው የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱ ፈጣን፣ ጥራት ያለው እና በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ዶክተር በከር በበጀት ዓመቱ የሥልጠና ጥራት እና አግባባነትን ለማረጋገጥ፣ በሙያ ደረጃና ሥርዓተ-ስልጠና ማሻሻል ላይ የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የትብብር ስልጠናውን ማጠናከር፣ የሥልጠና አጠናቃቂዎችን ከሥራ ጋር ማስተሳሰር፣ የምዘና ስርዓት ውጤታማነት ከብቃትና ጥራት ጋር ማያያዝ፣ የሴት ሰልጣኞች እና አመራሮችን በልዩ ሁኔታ ማሳደግ እንዲሁም የውስጥ ገቢን ማሳደግ ላይ በአሰራር እና በፖሊሲ ታግዞ መሄድ ይገባል ብለዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነቢሃ መሀመድ በበኩላቸው÷ ከክህሎት ልማቱ እና ከኢንዱስትሪ ሰላም ማስፈኑ አኳያ ቴክኒክና ሙያ ያለው ፋይዳ የማይተካ በመሆኑ ዘርፉ ልዩ ትኩረትን የሚሻ ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአቻ ተቋማት ጋር የጋራ ትስስር እና ትብብር ሥራዎችን መስራት በመጀመሩ እንደዘርፍ የሚሰጠው ትኩረት እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የሁሉም የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን÷ ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀማቸውን አቅርበው ውይይት እንደተካሄደበት ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.