Fana: At a Speed of Life!

2ኛው ዓመታዊ ፓርላሜንታዊ የምርምር ጉባዔ ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው ዓመታዊ ፓርላሜንታዊ የምርምር ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ጉባዔውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፥ የሀገርን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም አስተዳደራዊ ሁኔታዎች ለማሳደግ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ ጊዜውን የዋጀ ጥናትና ምርምር ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ምክር ቤቱ የሚያከናውናቸውን መደበኛ ሥራዎች በምርምርና በጥናት በማስደገፍ ችግር ፈቺ ሕጎችን ለማውጣት እንዲሁም የአሠራር ለውጥ የሚፈልጉ አሳሪ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ለማስተካከልም ጥናትና ምርምር እንደሚስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ሂደት የተደገፈ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ችግሮችን መፍታት ለአገር ይጠቅማል ነው ያሉት፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ፓርላማው የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን ለመቆጣጠር፣ ለመከታተልና ለመደገፍ በምርምርና በጥናት በተደገፉ ሥራዎች መታገዝ እንዳለበት ጠቁመው÷ የትምህርት ሚኒስቴር ፓርላማውን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ዶክተር ሄኖክ ስዩም በምርምር ሥራዎች የሚገኙ አዳዲስ የምርምር ግኝቶችንና ምክረ ሐሳቦችን ምክር ቤቱ በመቀመር ለሚያወጣቸው ሕጎች በግብዓትነት እንደሚጠቀምባቸው ገልጸው÷ የጥናትና ምርምር ሥራዎቹም ሀገርንና ትውልድን ወደፊት የሚያሻግሩ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ÷ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጡ ተመራማሪዎች፣ የሲቪክ እና የሙያ ማኅበራት እንዲሁም የምክር ቤቱ አባላት እና ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.