Fana: At a Speed of Life!

በ20 ሚሊየን ዶላር የተከናወኑ የኤሌክትርክ ሃይል የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ20 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተከናወኑ የኤሌክትርክ ሃይል የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በአገልግሎቱ የፕሮጀክት ኃላፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡

በአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች በሚገኙ ስምንት ማከፋፈያ ጣቢያዎች የማስፋፊያ እና አቅም ማሳደግ ሥራዎች ተከናውነዋል።

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዐቢይ አታኩሬ እንደገለፁት ፥ በቃሊቲ 1 ፣ በሰበታ 1 እና 2፣ በለገጣፎ፣ በገላን፣ በቢሾፍቱ 3፣ በሆለታ እና ኢላላ ገዳ የተሰሩት የማስፋፈፊያና አቅም ማሳደግ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።

በስምንቱም ጣቢያዎች ላይ የተለያየ አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች መተከላቸውንና ቀድሞ የነበራቸውን አቅም የሚያሳድግ ሥራ መሰራቱን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ለማስፋፊያ ሥራው የወጣው 20 ሚሊየን ዶላር የተሸፈነውም የአፍሪካ ልማት ባንክ በብድር ከሰጠው 40 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ዐቢይ ገለፃ ፥ በጣቢያዎቹ ላይ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የአቅም ማሳደግ ስራ ቢሰራም÷ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሰበታ 1 እና 2፣ ቃሊቲ 1 ፣ ገላን ፣ እና ኢላላ ገዳ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውጪ መስመሮቹን እስካሁን መጠቀም አልጀመረም።

በመሆኑም መስመሮችን በአፋጣኝ ዝግጁ በማድረግ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አቶ ዐቢይ ጠይቀዋል።

በማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ላይ የተሰራው ማስፋፊያ ለኢንዱስትሪዎችና ለተጠቃሚው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.