Fana: At a Speed of Life!

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰላምን ለማስፈን መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰላምን ለማስፈን መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ፡፡

4ኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በጎንደር ከተማ ተጀምሯል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ማህበረሰብ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር÷ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ በጽንፈኞችና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ባለሙ እኩይ ኃይሎች በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል፡፡

በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍንና ዜጎች በሰላም እንዲኖሩ መንግሥት አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

4ኛው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችንን በተሳካ መንገድ በመከወን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ዕቅዳችንን ልናሳካ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማድረግ ህልማችንን ለማሳካት ሁሉም ሰው በየተቋማቱ እና በመኖሪያ ቤቱ ችግኞችን እንዲተክል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዛሬ በክልሉ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም÷ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ የደንን ጥቅም በውል ተገንዝቦ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ደን ሊፈጥር ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ፥ ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች ነገ ለኢትዮጵያ ልብስ፤ ለሕዝቦቿ ደግሞ እስትንፋስ ናቸው ብለዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ100 ዓመታት በፊት በደን ልማት የተሸፈነች ውብ ሀገር እንደነበረች አስታውሰው÷ ዛሬ በሕገ ወጥ የደን ምንጣሮ ምክንያት የተራቆተ መልክዓ ምድር እንዲኖራት መገደዷን ገልጸው ፤ የደን ጥቅም የአየር ንብረትን ከመታደግ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ከደን ልማት የሚገኙ ተዋጽኦዎችን በዋና ግብአትነት እንደሚጠቀሙም አመላክተዋል፡፡

በተለይ አፈርን በመጠበቅና ለከብቶች መኖ በማምረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፥ ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች ነገ ደን ሆነው እና ፍሬ አፍርተው ለሕዝብ ጥቅም ከመዋላቸው በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት በመዋል ለሀገር ውስጥና ለውጭ ኤክስፖርት አቅርቦት ይውላሉ ብለው ፤ በተለይ ቡና ሽጠን ጣውላ ከውጭ የምናስገባበትን ሂደት ያስቀራሉ ነው ያሉት፡፡

የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ለማልበስ ቁርጠኛ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዶክተር ሙላቱ ፥ ጎንደርና አካባቢዋን በአረንጓዴ ልማት ለማልበስ የተጀመረው እንቅስቃሴም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ለዚህም ሁሉም ህብረተሰብ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.