Fana: At a Speed of Life!

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከ5 ሺህ 800 በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አበረከቱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 5 ሺህ 865 መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዛሬ አበርክተዋል፡፡

”ሚሊየን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ’ በሚል መሪ ቃል ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በሚከናወነው የመጻሕፍት ማሰባሰብ ንቅናቄ የተለያዩ ተቋማትና ዜጎች ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

በዚህ መሰረትም ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ያሰባሰቧቸውን መጻሕፍት በዛባ ዕለት አስረክበዋል፡፡

መጻሕፍቱን የዩኒቨርሲቲውና የኮሌጁ አመራሮች ለአዲስ አበባ የባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የፅህፈት ቤት ኃላፊ ፈይሳ ፈለቀ ማስረከባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሐረማያ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል የሱፍ÷ 4 ሺህ 334 የተለያዩ የምርምር፣ የፍልስፍና እንዲሁም የታሪክ ይዘት ያላቸው መጻሕፍትን ለአብርሆት ማስረከባቸውን ተናግረዋል ።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ግሩም ግርማ ÷ኮሌጁ ከተማሪዎች፣ ከሰራተኞች እና ከተቋሙ ወዳጆች ያሰባሰባቸውን 1 ሺህ 531 መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.