Fana: At a Speed of Life!

ጥቃት በማድረስ ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ ጥቃቶች ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ጸጋ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በማንነት ሽፋንና በተለያየ መልኩ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ተሳትፎ በሚያደርጉ አካላት ላይ እየተወሰደ ስላለው እርምጃና ሙስናን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሃን ወገኖች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት አውግዘዋል፡፡
በወንጀሉ ፈፃሚዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድና ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ሃይማኖትንና ማንነትን ሽፋን በማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደረሰ ጥቃት ተሳትፎ የነበራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ከፌደራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ምርመራ መቀጠሉንም አንስተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንጹሃን ላይ በተፈፀመው ቃጠሎ በወንጀሉ ተሳትፎ አላቸው ተብለው በተጠረጠሩ የጸጥታ አካላት ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወደ ሌላው ለመሄድ መጀመሪያ እራስን መገምገምና ማጥራት ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል በሚል የሙስና ተግባር ዝንባሌን ለመረዳት በተቋሙ ውስጥ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል።
የተካሄደው ጥናት ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው÷ ለአብነትም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የልማት ተነሽ ያልሆኑ 29 ግለሰቦች ላይ ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ያለአግባብ በመንግስት ገንዘብ ላይ ምዝበራ እንዲፈጸም ባደረገ ግለሰብ ላይ ክስ መመስረቱን ገልጸዋል።
ለተቋሙ የቀረቡ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ሶስት የተቋሙ ሰራተኞች የሙስና ወንጀል ሲፈጽሙ ተገኝተው የክስና ምርመራ ተግባር እየተካሄደ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት፡፡
በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በሃይማኖትና በማንነት ሽፋን ተደርገው የተለያየ አጀንዳ ባላቸው የጥፋት አቀናባሪዎች በተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ አብዛኞቹ እልባት እየተሰጣቸው ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.