Fana: At a Speed of Life!

የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦትን የሚደግፈው የአፍሪካ ልማት ባንክ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማገዙን የባንኩ ፕሬዚዳንት ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 18 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦትን የሚደግፈው የአፍሪካ ልማት ባንክ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እያገዘ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት ገለፁ።

ፕሬዚዳንቱ አኪንውሚ አዴሲና በቡድን 7 ሀገራት ስብሰባ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልክታቸው በሩሲያና ዩክሬን ግጭት ምክንያት ብዙ ሀገራት ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡

በዚህም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝብ ያላት አፍሪካ የገፈቱ ቀማሽ መሆኗን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፥ አሁን ላይ ለአፍሪካ የምግብ እርዳታ መስጠት ላይ ሳይሆን አላማ ማድረግ ያለብን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

አፍሪካ በአሀኑ ሰዓት በቋቷ እንዲኖር የምትፈልገው የምትመገበው ምግብ ሳይሆን የምታመርተው ዘር ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች አስፈላጊው ቴክኖሎጂ ቢቀርብላቸው አፍሪካን መመገብ ይችላሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ግብርና ትራንፎርሜሽን በተሰኘው መርሀ ግብር በሁለት አመት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ምርጥ ዘር 12 ሚሊየን ለሚሆኑ የአፍሪካ አርሶ አደሮች እንደቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለአርሶ አደሩ ሙቀትን መቋቋም የሚችል የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ በመደረጉ በሁለት አመታት ውስጥ 675 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የተቻለ ሲሆን፥ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርትንም በ80 በመቶ እንዲቀንስ ማስቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በባንክ በሚደረግላት ድጋፍም ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ከ1 ነጥብ 2 እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የሚደርስ ስንዴ ለኬንያና ጅቡቲ ለመላክ ማቀዷን ነው የተናገሩት።

የሩሲያና ዩኩሬን ግጭት በምግብ ዋስትና ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመመከትም የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአስቸኳይ የምግብ ምርት አቅርቦት የሚውል 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ማፅደቁን ተናግረዋል፡፡

የአስቸኳይ የምግብ ምርት አቅርቦት እቅዱም ከአፍሪካ ህብረት ጋር በጥምረት የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.