Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ከአሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ 25 ፕሮፌሰሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ ከሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ 25 ፕሮፌሰሮች ጋር ውይይት ማካሄዳቸውን ገለጹ፡፡

አምባሳደር ስለሺ ÷በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅለል ያለ ውይይት ከምሁራኑ ጋር ማካሄዳቸውን የጠቆሙ ሲሆን በተለይም በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በግጭቶች፣ በምግብ ዕጥረት እንዲሁም በፍልሰት ላይ ሃሳቦችን መለዋወጣቸውን አንስተዋል፡፡

ችግሮቹ ህዝብ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ ለመቀነስ እና ዕልባት ለመስጠት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችም መነሳታቸውን አምባሳደር ዶክተር ስለሺ ጠቅሰዋል፡፡

በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብም በሀገራቱ መካከል የቆየውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ እየተወጣ ያለውን ሚናም አስረድተዋል።

ምሁራኑ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የአፍሮ-አሜሪካውያንን ስኬት ያነሱ ሲሆን ፣ በአሜሪካ ከነሱ በሚጠበቅ ማናቸውም ነገር የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደር ዶክተር ስለሺ ÷ ምሁራኑ ስለ ኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ስለሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት አድንቀው ይህን መሰል ግንኙነት የሀገራቱን ወዳጅነት እና ትብብር ያጠናክራል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች መካከል የሁለትዮሽ መርሃ-ግብሮች ፣የጋራ የምርምር ሥራዎች እና በተማሪዎች መካከል የሚኖሩ የልምድ ልውውጦችን ማካሄድ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.