Fana: At a Speed of Life!

የህግ ማስከበሩን ስራ ይበልጥ በማጠናከር የተረጋጋች አገር ለመገንባት የተጀመረው ስራ ይቀጥላል-የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህግ ማስከበሩን ስራ ይበልጥ በማጠናከር የተረጋጋች አገር ለመገንባት የተጀመረው ስራ የሚቀጥል መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡

አባላት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ጥቅማቸው የቀረባቸው የውስጥ ተላላኪዎች ከውጭ ጠላቶች ጋር ህብረት በመፍጠር በዜጎች ሰላምና ደህንነት ላይ አደጋ ለማድረስ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የጥቃቱን ተጎጂዎች መደገፍና ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኦሞድ ኡጁሉ÷ በለውጡ ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ሰለማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመፈጸም ለውጡን ለመቀልበስ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነት በንጹሃን ዜጎች ደም ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በተመሳሳይ ሌላኛዋ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ቡዜና አልቃድር በበኩላቸው÷ የተዳከመችና የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት የሚሹ የውጪ ጠላቶችና የውስጥ ተላላኪዎች ሰላማዊ ዜጎችን በማጥቃት ለውጡ ይዞት የመጣው ትልም አውን እንዳይሆን መስራታቸውን አመላክተዋል፡፡

የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ አቶ አብዱረህማን እድሪስና አቶ ኦድሪን በድሪ÷ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አዝማሚያዎች በዜጎች ሰላምና ደህንነት ላይ እንቅፋት መፍጠራቸውን አንስተዋል፡፡

የውጪ ጠላቶች እና የውስጥ ተላላኪዎች የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አካሄዶች ይበልጥ እንዲስፋፉ ተቀናጅተው በመስራት በሰላማዊ ዜጎች ህይወት ላይ አደጋ እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡

በዚህም ዜጎች የሰላምና ደህንነት ጥያቄ በስፋት ሲያነሱ መቆየታቸውን ጠቅሰው÷ መንግስት በተቀናጀ መልኩ የህግ ማስከበር ስራ በማከናወን ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቁ ስራ በተቀናጀ መልኩ እንዲከናወን አቅጣጫ ማስቀመጡን እና ከዚህ አኳያ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አመራሮች ተጠያቂ እንደሚሆኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.