Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎችና የምግብ ዋስትና ችግር ላለባቸው ወረዳዎች 54 ተሽከርካሪዎች ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎችና የምግብ ዋስትና ችግር ላለባቸው ወረዳዎች የሚሆኑ 54 ተሽከርካሪዎችን ከግብርና ሚኒስቴር ተረከበ።

ድጋፉ በክልሉ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰባት ዞኖችና 54 ወረዳዎች የሚውል ነው ተብሏል።

ለሰሜን ወሎ ዞን 11 ወረዳዎች ፣ ደቡብ ወሎ ዞን 20 ወረዳዎች፣ ዋግ ኸምራ ዞን 7 ወረዳዎች፣ ሰሜን ሽዋ ዞን 6 ወረዳዎች፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን 5 ወረዳዎች እና ለሌሎች 5 ወረዳዎች ድጋፉ ተደርጓል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በርክክቡ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት ፥ በተለያዩ ቦታዎች በሚደርሱ ጉዳቶችና ጥቃቶች የማይበገር ኢኮኖሚ እንዲኖረን ግብርናውን በማገዝ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ ተደራሽ ማድረግና ጉዳት በደረሰባቸው ላይ ደግሞ ሊያግዙ የሚችሉ መሰል ድጋፍ ማድረግ ዋናው መንገድ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ጉዳት በደረሰባቸው 54 ወረዳዎች ላይ ተደራሽ እንዲሆኑ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኙ ተሽከርካሪዎችን ለታለመላቸው የግብርና ስራ ብቻ ለማዋል ሃላፊነት መውሰድ ያስፈልጋልያሉት ሃላፊው ፥ ይሄ ሲሆን ለችግሮቻችን መፍትሄ ሰጥተን ያሰብነውን ማሳካት እንችላለን ብለዋል።

በክልሉ ላሉ ሌሎች ወረዳዎችም መሰል እገዛዎችን ለማድረግ በቀጣይም ስራዎች እንደሚከወኑም አመላክተዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መንግስቱ ድልነሳው እንዳሉት ፥ ድጋፉ በአማራ እና አፋር ክልሎች የደረሰውን ጉዳት መሰረት መነሻ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከደረሰው ጉዳት በመውጣት ወደ ተግባር ለማስገባት በግብርና ሚኒስቴር ከሚደረጉ የተለያዩ ድጋፎች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

የተሽከርካሪ ድጋፉ በጦርነቱ ጉዳት ውስጥ ላለፉ ዞኖችና ወረዳዎች የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ለሚከውኗቸው ስራዎችም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋልም ነው ያሉት።

ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ የተሽከርካሪ ድጋፍ ከማድረግም ባለፈ የግብርና ግብአትና ሌሎች የቢሮ ስራ መከወኛ ቁሳቁሶችንም ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ጠላት ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ያለው ትልቅ የድጋፍ ክትትል ያስፈልጋል ያሉት የጽህፈት ቤት ሃላፊው ፥ ማህበረሰቡን አረጋግቶ ወደ ግብርና ልማት ስራ በማስገባት የጠላትን ፍላጎት ማምከን ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

በይስማው አደራው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.