Fana: At a Speed of Life!

ለአማራ ክልል መልሶ ማቋቋምና ግንባታ የሚውል የ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በክልሉ ለመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ድጋፍ የሚሆን 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የእርዳታ ስምምነት ፕሮጀክት ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር አደረገ።

ስምምነቱን የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጥላሁን መሐሪ እና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ቱርሃን ሳለህ ተፈራርመዋል።

ዶክተር ጥላሁን በዚህ ወቅት፥ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በክልል ደረጃ ወደ አማራ ክልል ገብቶ የልማት ድጋፍ ሲያደርግ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸው፥ ድጋፉ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት በኩል የክልሉን ሥራ የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

አማራ ክልል የደረሰውን ውድመት በክልሉ አቅም ብቻ መልሶ ለማቋቋም አስቸጋሪ በመሆኑ ሌሎች ረጅ ድርጅቶችም ተባባሪ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበው ፥ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት የክልሉን ጉዳት ተረድቶ ለመደገፍ በመምጣቱም አመስግነዋል።

የልማት ድርጅቱ ዋና ተጠሪ ቱርሃን ሳለህ በበኩላቸው ፥ በአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት ብዙ የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን እንደተገነዘቡ ገልጸው፥ ይህንን መልሶ ለመገንባትና ለሕዝብ አገልግሎት ለማዋልም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ይሠራል ብለዋል።

በአማራ ክልል በጦርነት ውስጥ በነበሩ ዞኖች የሚገኙ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም የፍትሕና የፀጥታ ተቋማት ወድመዋል ያሉት ዋና ተጠሪው ፥ የፍትሕ ተቋማትን ሥራ በመደገፍ ክልሉ ሰላሙ የተረጋገጠ እንዲሆን በጋራ እንደሚሠሩ መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።

በጦርነቱ አነስተኛ የንግድ ሥራቸው የተቋረጠባቸውና ሥራ አጥ የሆኑ ዜጎችን እንደሚደግፉም ተናግረዋል።

የተደረገው ድጋፍም 14 የመስክ ተሽከርካሪ፣ ጥሬ ገንዘብና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች የተካተቱበት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ፥ አጠቃላይ የድጋፉ ስምምነት መጠኑም በገንዘብ ሲተመን 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር እንደሆነ ተገልጿል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.