Fana: At a Speed of Life!

አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚ መስክ የነበሩ ስብራቶችን መቅረፍ ያስቻለ ነው – የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግድ አፈጻጸምን ጨምሮ በኢኮኖሚ መስክ የነበሩ ስብራቶችን መቅረፍ ያስቻለ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዳሉት÷ ፓርቲው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጠናከርና ፈተናዎችን ደግሞ ተባብሮ በመፍታት ለመሥራት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች ተግባራዊ የሆኑ የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያን ከውደቀት የታደገ ውጤት ማስመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ማሞ ምህረቱ ÷በለውጡ ዋዜማ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመንግሥት ሰራተኞች እንኳን ደመወዝ መክፈል በማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት በመንግሥት ወጪ በሚገነቡ የመሰረተ-ልማት ሥራዎች ላይ የተንጠለጠለ ስለነበር ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለም ጠቁመዋል፡፡

የብድር ጫና፣ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ዝቅተኛ የወጪ አፈጻጸም ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እውን መሆን ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ÷ ከለውጡ በፊት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ከማስተዳደር አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንደነበረች ይናገራሉ፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የውጭ ብድር ማግኘት በማትችልበት ደረጃ ደርሳ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

ዶክተር ግርማ አመንቴ እና ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢ በበኩላቸው÷ በተለያዩ መስኮች የተከናወኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ከወዲሁ ውጤታማ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ግርማ÷ ከለውጡ በፊት “ግብርና መር ኢንዱስትሪ” የሚል ስትራቴጂ በወረቀት ላይ ከማስቀመጥ ባለፈ ግብርናው ድጋፍ ሲደረግለት እንዳልነበር እና አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ስኬታማ ሥራዎች እንዲከናወኑ መደረጉን አንስተዋል፡፡

አቶ ማሞ ምህረቱ÷አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የንግድ ብድሮችን በማስቀረት የእዳ ጫናው ከአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነጻጸር ከነበረበት 33 በመቶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ ከባንኮች የተሰበሰበ ቁጠባን ወደ 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር እንዲሁም የወጪ ንግድ አፈጻጸምም ካለፈው ዓመት በ14 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው በበኩላቸው÷በቡና ምርት ብቻ ባለፉት 11 ወራት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቁመው÷የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በገቢ አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ እምርታ መመዝገቡንም አንስተዋል፡፡

ዶክተር ግርማ አመንቴ ÷አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ቢችልም የኑሮ ውድነቱ አሁንም የኢኮኖሚው ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከዚህ አኳያ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሩ ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በተለይ በግብርናው መስክ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የኑሮ ውድነት ጫናውን ለመቀነስ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.