Fana: At a Speed of Life!

የሀገሪቱን የውሃ ሀብት በማልማት ለዜጎች ጥቅም እንዲውል ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በማስፈን የሀገሪቱ የውሃ ሀብት ለሀገሪቱ ዜጎች ማኅበራዊና፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዲውል ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተፋሰስ እቅድ ዝግጅት ላይ ከባለያሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ ምክከሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት÷ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በማስፈን የሀገሪቱን የውሃ ሀብት ለሀገሪቱ ዜጎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዲውል ማድረግ ይገባል፡፡

በዓለም ላይና በሀገራችን እየተከሰተ ያለውን ተደጋጋሚ ድርቅና ተያያዥ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የብዙ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም የመስኖ ልማትና የኃይል ተደራሽነት ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው÷ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ማስፈንና ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው በወላይታ ሶዶ፣ በመደወላቡ እና በዲላ ዩኒቨርሲቲዎች በቅደም ተከተል እየተሠሩ ያሉትን የኦሞ ጊቤ፣ ዋቢ ሸበሌ እና ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ቤዝን ፕላን ዝግጅት የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገምና ለዩኒቨርሲቲዎቹ ተጨማሪ ግብዓትና አቅጣጫዎችን ለመስጠት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የባሮ አኮቦ ተፋሰስ የቤዚን ፕላን ዝግጅትን ለማስጀመር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሚዘጋጁት የተፋሰስ ዕቅዶች በተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤት እየጸደቁ ወደ ትግበራ የሚገቡ ይሆናል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.