Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር ሰላማዊ አማራጮች እንዲታዩ የብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር የሰላም አማራጮች እንዲታዩ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ውሳኔ አሳለፉ።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እና የፍትሕ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በሰጡት መግለጫ÷ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ያካሄዱት ስብሰባ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ኮሚቴዎቹ በሰላምና ደህንነት፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ፣ በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው÷ በቅርቡ በጋምቤላና በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት መወገዙን ተናግረዋል።
የተጀመረው የሕግ ማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመው÷ በተወሰደው እርምጃም በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንም ነው የተናገሩት።
በንፁሃን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋም መንግሥትና ሕዝብ በልማት ላይ ያላቸውን ትኩረት ለማዛባት እንደሆነ ጠቅሰው÷ በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌትና የሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጅማሮን ለማደናቀፍ ነው ብለዋል።
አርሶአደሩ የመኸር እርሻ ሥራ ላይ ተረጋግቶ እንዳይሠራ የታቀደ እኩይ ድርጊት መሆኑን ገልጸው÷ የሽብር ቡድኖቹ ድርጊት የትኛውንም ብሔር አይወክልም ነው ያሉት፡፡
መንግሥትና ሕዝብ በጋራ በመቀናጀት÷ የጠላትን ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማ ይቀለብሱታልም ነው ያሉት አቶ አደም፡፡
በኮሚቴዎቹ ስብሰባ የውስጠ ፓርቲ ጉዳዮች መገምገማቸውን ጠቁመው÷ ብልጽግና ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱ የተጠናከረ ፓርቲ መሆኑን ገልጸው ÷ ውስጠ ፓርቲ ስነ ምግባሩም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል ኢዜአ ዘግቧል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችና ጉድለቶች መገምገማቸውን ገልጸው÷ ማክሮ ኢኮኖሚው ያጋጠመውን መዛባት ለማረጋጋት ሀገር በቀል ሪፎርም በማድረግ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በሰጡት መግለጫ÷ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር የሰላም አማራጮች እንዲታዩ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ውሳኔ ማሳለፋቸውንም አመላክተዋል፡፡
በዚህም ጦርነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተገዶ የገባበት በመሆኑ÷ በጦርነት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ፣ ሙሉ ትኩረት በልማት ላይ እንዲሆን ለማድረግ፣ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ለማሻሻል፣ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በማሰብ ኮሚቴዎቹ የሰላም አማራጮች እንዲታዩ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
የሰላም አማራጩ ወይም ንግግሩ ሲካሄድም÷ ሕገ መንግሥታዊነትን ባከበረ ፣ የሀገርን መሠረታዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መሆን እንዳለበትና ንግግሩም በአፍሪካ ሕብረት መሪነትና አስተባባሪነት መመራት እንዳለበት ውሳኔ ማሳለፉን አብራርተዋል፡፡
ለሰላም ቅድሚያ ተሰጥቶ መሥራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ÷ ማንኛውም ፀብ ጫሪነትና ትንኮሳዎች ካሉ ለእነዚህ ትንኮሳዎች አፀፋ የሚሰጡ ተቋማት ዝግጁነት እንዲጠናከርም ነው ውሳኔ ያሳለፉት ኮሚቴዎቹ፡፡
ለዚህም የፀጥታና የደህንነት ተቋማት በሙሉ ዝግጁነት በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ውሳኔ ማሳለፉንም ነው ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የገለጹት፡፡
አቶ አደም ፋራህ በመግለጫቸው÷ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች በመደምሰስ የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ እንሠራለን ብለዋል፡፡
የጠላት ሚዲያ የተዛባ መረጃ በማስተጋባት ውዥንብር እየፈጠሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.